የሦስትዮሽ የኃይል ሽያጭ ሥምምነት ተፈረመ

የሦስትዮሽ የኃይል ሽያጭ ሥምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  ኃይል፣ የታንዛኒያ የኤሌክትሪክ አቅራቢ ኩባንያ እና የኬንያ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኩባንያ ሲያካሂዱት የቆዩትን የሦስትዮሽ የኃይል ሽያጭ ድርድር አጠናቀው ስምምነት ላይ ደረሱ።

ስምምነቱ በኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ላይ ያተኮሩ የህግ፣ የኮሜርሻል እና የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ  መሠረት ያደረገ እንደሆነ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

የሦስትዮሽ ድርድሩን መጠናቀቅ ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር የኃይል ሽያጭ እንዲሁም ኬንያ ከታንዛንያ ጋር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የኪራይ ውል ሥምምነት ተፈራርመዋል።

የኃይል ሽያጭ ሥምምነቱ በሀገራቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ፀድቆ ከሚያዝያ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ታከናውናለች።

ሥምምነቱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህግ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ መርክነህ ይገዙ፣ የኬንያ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኩባንያ (KETRACO) ስትራቴጂ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጎድፍሬይ ካሪዩኪ እና የታንዛኒያ የኤሌክትሪክ አቅራቢ ኩባንያ (TANSCO) የዕቅድ፣ ምርምር እና ኢንቨስትመንት ምክትል ዳይሬክተር ሚስስ ሬንታ ንድጌ ተፈራርመዋል።

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህግ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ መርክነህ ይገዙ ሀገራቱ የሦስትዮሽ ድርድሩን ለማሳካት ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሦስትዮሽ ሥምምነቱ ከኃይል ሽያጭ ባለፈ ለቀጣናዊ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ነው የገለፁት።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል የኃይል ሽያጭ ውል ሥምምነት ተፈርሞ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ያወሱት ዳይሬክተሩ ከኃይል ሽያጩም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

እንደ አቶ መርክነህ ገለፃ ሦስቱ ተቋማት የህግ፣ ኮሜርሻልና ቴክኒክ ጉዳዮች እንዲሁም በጋራ ተባብረው በሚሰሩበት ዙሪያ በጥልቀት ገምግመው የኃይል ሽያጭ ሥምምነቱን አፅድቀዋል።

የሦስትዮሽ ሥምምነቱ ኢትዮጵያ በኬንያ በኩል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችላትን መብት የሚሰጣት መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

የታንዛኒያ የኤሌክትሪክ አቅራቢ ኩባንያ የዕቅድ፣ ምርምር እና ኢንቨስትመንት ምክትል ዳይሬክተር ሚስስ ሬንታ ንድጌ ድርድሩ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ገልፀው ተቋማቱ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የኬንያ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኩባንያ ስትራቴጂ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጎድፍሬይ ካሪዩኪ በበኩላቸው የሦስትዮሽ የኃይል ሽያጭ ድርድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ የሦስቱ ተቋማት ባለሙያዎችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top