የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሚያከናውናቸው የኃይል መሰረተ ልማት ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች ጋር የአሶሳ ማከፋፈያ ጣቢያ የመሬት ይዞታ ለውጥን በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እና የንብረት አስተዳደር መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ከሊል ሽፋ ከማከፋፋያ ጣቢያው የመሬት ይዞታ ለውጥ ጋር ተያይዞ በተቋሙ በኩል የሚነሱ ቅሬታዎችንና የማከፋፈያ ጣቢያው የኃይል አቅርቦት በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።
የሥራ ኃላፊዎቹ በገለጻቸው የመሬት ይዞታ ለውጡ በአሶሳ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ በሚከናወነው የማስፋፊያ ሥራ፣ በጣቢያው ደህንነት እና በኃይል አቅርቦቱ ላይ ችግሮችን የሚያስከትል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአሶሳ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱልካሪም አብዱራሂም የመሬት ይዞታው ለውጥ በከተማው እየተካሄደ ካለው የኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የተከሰተ መሆኑንና ለማከፋፈያ ጣቢያውም ምትክ መሬት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
የርዕሰ መስተዳድሩ የመሠረተ ልማት ዘርፍ አማካሪ አቶ አበራ ባያታ በበኩላቸው ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ – አሶሳ ለሚዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ እና በነባሩ የአሶሳ ማከፋፈያ ጣቢያ ውስጥ ተቋሙ ለሚያከናውናቸው የማስፋፊያ ሥራዎች የክልሉ መንግስት ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ከማከፋፈያ ጣቢያው የመሬት ይዞታ ለውጥ ጋር ተያይዞ እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎች በግንኙነትና በመረጃ ክፍተት የተፈጠሩ ናቸው፡፡
ለክልሉ ሁሉን አቀፍ እድገት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታሁን ከተቋሙ ጋር በትብብርና በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ከተቋሙ ጋር በቅርበት ተባብሮ ለመስራት አሶሳ ከተማ ውስጥ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቢሮ እንዲያደራጅ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

