በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ ምዕራብ ሪጅን ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፍያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ባለፉት ስድስት ወራት በስምንት ማከፋፈያ ጣቢያዎች አስቸኳይ የጥገና ሥራዎችን ማከናወኑን ገለጸ፡፡
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ሲሳይ እንደገለጹት ሪጅኑ የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት የሚያሳድጉ በዕቅድ ላይ የተመሰረቱ የጥገና ሥራዎች በማከፋፈያ ጣቢያዎችና በማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ያከናውናል፡፡
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በስምንት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ አስቸኳይ የጥገና ሥራዎችን መስራቱን ተናግረዋል፡፡
በሚዛን፣ በጅማ አንድና ሁለት፣ በመቱ፣ በበደሌ እና ሌሎች ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ከፓወር ኬብል፣ ከትራንስፎርመር፣ ከብሬከርና ከባትሪ ጋር በተገናኘ የተከሰቱ የአስቸኳይ ጥገናዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ከግልገል ጊቤ 1 ኃይል ማመንጫ – ሰኮሩ ማከፋፈያ ጣቢያ በተዘረጋው ባለ 400 ኬሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር ላይ በስድስት ቦታዎች የኮንዳክተር የጥገና ስራ ተከናውኗል፡፡
የጥገና ሥራው በማከፋፈያ ጣቢያዎቹና ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በተደጋጋሚ ያጋጥም የነበረውን የኃይል መቆራረጥና በየጊዜው የሚከሰቱ የአስቸኳይ ጥገና ሥራዎችን መቀነሱን ጠቁመዋል።
በሪጅኑ የሚገኙ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለማዘመን በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንና በደሌ 33 ኪሎ ቮልት ስዊች ጊር በጂአይኤስ የመቀየር ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
በመቱ፣ በጅማ እና ግልገል ጊቤ 1 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ደግሞ ለማስፋፊያ ሥራው የሲቪል ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ሪጅን አስራ አንድ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና 1900 ኪሎ ሜትር ሴርኪዩት የማስተላለፊያ መስመሮች ያስተዳድራል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”