የብድርና ቁጠባ ማህበሩ የምስጋና ፕሮግራም አካሄደ

የብድርና ቁጠባ ማህበሩ የምስጋና ፕሮግራም አካሄደ

የኢትዮ ኤሌክትሪክ ገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እየተደረገለት ላለዉ ቁሳዊና ቴክኒካል ድጋፍ ምስጋና አቀረበ፡፡

ማኅበሩ ባዘጋጀዉ የምስጋና ፕሮግራም አስተዋጽኦ ላደረጉለት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲሁም በሁለቱ ተቋማት ለሚገኙ ለተለያዩ የሥራ ክፍሎች የእዉቅና ምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አንበስ ግዛቸዉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማህበሩ እያደረገ ስላለዉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አመስግነዉ ስለማህበሩ ቀጣይ ዕቅዶች ይፋ አድርገዋል፡፡

የማህበሩ የብድር ጣሪያውን ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ለማሳደግ እና የማህበሩን አሰራር የሚያዘመንና የሚያሳልጥ አሰራር ለመዘርጋት የተለያዩ ጥረቶች መጀመራቸውን የቦርድ ሰብሳቢዉ አስታዉቀዋል፡፡

በማህበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ የማህበሩ አባለትን ተቋማቱ ከሚገኙባቸው የሥራ ቦታዎች በተመረጡ ተወካዮቻቸዉ እንዲሳተፉ የሚያስችል አሰራር እንደሚተገበር ጠቁመዋል፡፡

ለሆነም በቅርቡ የቦርዱ ስራ አመራሮች ጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊ ተወካይ አባላትን ለማስመረጥ በሚሄዱባቸው የስራ ቦታዎች የሚመለከታቸው ኃላፊዎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡

እንደ አቶ አንበስ ገለፃ አዲስ የማህሩ አባል ለመሆን የሚፈልግ ሠራተኛ ቀደም ሲል ይጠየቅ የነበረዉን የደመወዙን ስድስት በመቶ የመመዝገብያ ክፍያ ከጥር 8 እስከ መጋቢት 8 2017 ዓ.ም ድረስ ከክፍያ ነጻ መሆኑን ገልጸዋል። ሠራተኛዉ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ የማህበሩ አባል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ባስተላለፉት መልእክት ማህበሩ ጽ/ቤቱን እዚህ መክፈቱ የአግልግሎት ፋለጊ ሰራተኞችን የስራ ጊዜ በመቆጠብ እርካታውን የሚያሳድግ በመሆኑ በቀጣይም ማህበሩን ይበልጥ ለማጠናከር ከማህበሩ ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ እንደሌሎች የቁጠባ እና ብድር ማህበራት ወደ ባንክ በሚያድግበትን እና የሠራተኛውን የመኖሪያ ቤት ችግር በሚቀርፍበት አግባብ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራም ተጠይቋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top