የጎረቤት ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር እየተሰራ ነው

የጎረቤት ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር እየተሰራ ነው

ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር እየሰራች መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ በታንዛኒያ በተካሄደው የአፍሪካ ታዳሽ ኃይል ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም ፍኖተ ካርታ 13 ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር እየሰራች ነው።

ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ለጅቡቲ፣ ለኬኒያና ለሱዳን ኃይል እያቀረበች መሆኑንና በቅርቡም ለታንዛኒያ ማቅረብ እንደምትጀምር ተናግረዋል።

በቀጣይም ያላትን እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን በኃይል ለማስተሳሰር የኢነርጂ ፖሊሲ ቀርፃ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ህዝቡ ንቁ ተሳታፊ መሆኑን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለአብነት አንስተዋል።

በሀገር ውስጥ ከኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ጋር የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትም መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህም በየዓመቱ ለ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤተሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር ተቋማዊ ሪፎርም በማድረግ፣ የግል ዘርፉን በማሳተፍና ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር በመስራት በዘርፉ ውጤት መገኘቱንም ገልፀዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top