
የግልገል ጊቤ 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በሙሉ አቅሙ ኃይል እንዲያመነጭ ለማድረግ የሚያስችል የጥገና ሥራ በራስ አቅም እየተከናወነ መሆናቸውን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለፁ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ሹመት በላቸው እንደገለፁት ውሃን ለመቆጣጠር በሚያገለግለው ሹል ጫፍ ባለው የብረት አካል ወይም ኖዝል ላይ የገጠመው የመበላት ችግር የዩኒት አራት ተርባይን በሙሉ አቅሙ ኃይል እንዳያመነጭ አድርጎት ቆይቷል።
በተርባይኑ ላይ ያሉት ስድስት የኖዝል ጫፎች (needle tip)፣ ኢንሰርቶች እና ሲሎች በመቦርቦራቸው፣ አንዱ ኖዝል ውሃ ወደ ተርባይን ማስተላለፍ በማቆሙ እና ሌሎች ኖዝሎች ደግሞ ውሃና ዘይት በማስረጋቸው በኦፕሬሽን ሥራው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንና የተርባይኑን የማመንጨት አቅም እስከ 45 ሜጋ ዋት ዝቅ ማድረጉን ጠቁመዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ተርባይኑ በሙሉ አቅሙ ኃይል እንዲያመነጭ ለማድረግ ጉዳት የደረሰባቸውን የኖዝል አካላት የመጠገን ሥራ እየተከናወነ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ኖዝሎቹን ከተርባይኑ ላይ የማውረድ፣ ፈትቶ የማፅዳት እና በሌላ ለመተካት የማስተካከል ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ አንዱን ኖዝል ተርባይኑ ላይ መልሶ የመግጠም ሥራ ሲናቀቅ ሌላ ተጨማሪ አንድ ኖዝል ደግሞ ለመልሶ ገጠማ ዝግጁ ተደርጓል።
የጥገና ሥራው በተርባይኑ ‘ቤሪንጎች’ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን እና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል እንደሚያግዝም ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል።
የጥገና ሥራው ከዚህ በፊት አገልግሎት የሰጡ እና ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ዕቃዎችን በጣቢያው ወርክሾፕ ላይ ማሻሻያ (modify) በማድረግ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ሹመት ጠቁመዋል።
በራስ አቅም እየተከናወነ ያለው የጥገና ሥራ የባለሙያዎችን በራስ የመተማመን አቅም ለማሳደግ እና በተቋሙ ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት ከማስቻሉም በተጨማሪ ተቋሙን ከተጨማሪ ወጪ እና ከውጭ ምንዛሪ እንደሚታደግ አስገንዝበዋል።
በተቋሙ ባለሙያዎች እየተሰራ ያለው ሥራ በውጭ ባለሙያዎች ቢሰራ ኖሮ ተቋሙን ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስወጣ ነበር ብለዋል።
በኖዝሎች ላይ እየተከናወነ ካለው የጥገና ሥራ በተጨማሪ በቀጣይ በዩኒት አራት ዋና የውሃ መክፈቻና መዝጊያ ቫልቭ (Main Inlet Valve) ላይ የጥገና ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ሹመት ጠቅሰዋል፡፡
በጣቢያው የኤሌክትሪካል መሀንዲስ አቶ ምስጋና ደቻሳ እና መካኒካል መሀንድስ አቶ ፋንታሁን እስከዚያ በበኩላቸው የኖዝል አካላቶቹ ከውሃ ጋር ወደ ተርባይኑ በሚገባ ደለልና ጠጠር እንዲሁም በአገልግሎት ጊዜ ምክንያት ሊቦረቦሩ መቻላቸውን ገልፀዋል።
በኖዝሎቹ ላይ የተስተዋለው ችግር የተርባይኑ የቁጥጥር ሥርዓት በማኑዋል እንዲከናወን ማስገደዱን ጠቅሰው ይህም ተርባይኑ ሲወጣ መልሶ ለማስገባት ተጨማሪ የሠው ኃይል እና ጊዜ እንዲጠይቅ አድርጎት እንደነበር አንስተዋል፡፡
ኖዝሎቹ ተጠግነው ወደ ሥራ ሲገቡ የዩኒቱን የማመንጨት አቅም ለማሳደግ፣ ወደ ተርባይኑ የሚገባውን ውሃ ለማመጣጠን፣ በውሃ አጠቃቀምና በቁጥጥር ስርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፉ እና የቆመውን ተርባይን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚወስደውን ጊዜ ለማሳጠር ያግዛል።
ከግንቦት 12 ጀምሮ እየተከናወነ ባለው የጥገና ሥራ ላይ የጣቢያው ባለሙያዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እና ከኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የተውጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት የሚገኙ ሲሆን ሥራውንም እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ነው።
በ2002 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጊቤ 2 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ እያንዳንዳቸው 105 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው አራት ተርባይኖች አሉት።
“ከካርቦን ልቀት የፀዳ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል!”









