የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በደጀን ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በመገኘት የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰበሳቢ፣ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የክልሉ እና የምስራቅ ጎጃም ዞን የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ የደጀን የማከፋፊያ ጣቢያን ጨምሮ በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ልዩ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰበሳቢ የተከበሩ አቶ አስቻለ አላምሬ በበኩላቸው የደጀን ኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የአካባቢውን ሕዝብ የኃይል አቅርቦት ችግር በዘላቂነት የሚፈታ እና ኢንቨስትመንትን የሚያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደጀን የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ተቆጣጣሪ እና አማካሪ አቶ ግርማ ብርሃኑ እንደገለጹት የማከፋፊያ ጣቢያው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመደበው 285 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል።
ግንባታው በግብዓት ችግር ምክንያት ከተቀመጠለት ጊዜ በላይ ቢወስድም የገጠሙት ችግሮች ተቀርፈው ሥራው በፍጥነት እየተከናወነ በመሆኑ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ወራት ግንባታውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
የደጀን ማከፋፈያ ጣቢያው ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥንድ ገቢ መስመር፣ አምስት ባለ 33 እና አምስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት።

