የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ባለፉት አስራ አንድ ወራት በጡረታ ለተሰናበቱ የማህበሩ አባላት ከ2.8 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈፀሙን አስታወቀ፡፡
የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ መኮንን ክፍሌ እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ በጡረታ ለተሰናበቱ ከ70 በላይ የማህበሩ አባላት በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ክፍያ ተፈፅሟል፡፡
በማህበሩ የነበራቸውን ቆይታ ታሳቢ ያደረገ ከአንድ እስከ ሁለት ወራት የደመወዝ ክፍያ የተፈፀመ መሆኑን የተናገሩት አቶ መኮንን ለአንድ የማህበሩ አባል 112 ሺህ ብር ክፍያ መፈፀሙን ነው ያስታወቁት፡፡
ሠራተኞች ለበርካታ ዓመታት ተቋማቸውን አገልግለው በጡረታ ሲሰናበቱ በክብር እና በምስጋና እንዲሰናበቱ በመደረጉ የጡረታ ተሰናባቾቹ ደስታቸውን ለማህበሩ በተደጋጋሚ እንደሚገልፁ ተናግረዋል፡፡
የማህበሩ አባላትን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ከዳሸን ባንክ የአለ በዱቤ ስምምነት በመፈራረም እና ሶስት ሚሊዮን ብር የዋስትና ገንዘብ ለባንኩ በማስያዝ የማህበሩ አባል ሠራተኞች የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችን በዱቤ እንዲገዙ እያገዘ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ማህበሩ ከዓመታዊ የደመወዝ ጭማሪ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ባሻገር የማህበሩ አባላትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን ለመፈፀም አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ መኮንን ገልፀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከ242 በላይ የተቋሙ ሠራተኞች ማህበሩን በአባልነት መቀላቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡
በ2007 ዓ.ም እንደ አዲስ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ከ4 ሺህ በላይ አባላት ያሉት አንጋፋ ማህበር ነው፡፡