ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፉት አስር ወራት ከ2 ሺ 700 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል አመንጭቷል

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፉት አስር ወራት ከ2 ሺ 700 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል አመንጭቷል

በሁለት ተርባይኖች ኃይል እያመነጨ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ2016 በጀት ዓመት አስር ወራት ከዕቅዱ የ26 በመቶ ብልጫ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱን የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ገለፀ፡፡

በዘርፉ የዕቅድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ሺፈራው እንደገለጹት ግድቡ በበጀት ዓመቱ አስር ወራት 2 ሺ 152 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት አቅዶ 2 ሺ 711 ጊጋ ዋት ሰዓት ማአመንጭቷል። ይህም ከዕቅዱ የ26 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።

ግድቡ የተሻለ ውሃ መያዙና ሁለቱ ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ መደረጉ ለዕቅድ አፈፃፀሙ ከፍ ማለት ምክንያት እንደሆነ ሥራ አስኪያጇ አስታውቀዋል።

እንደ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ገለፃ ባለፋት አስር ወራት በአጠቃላይ ከመነጨው የ16 ሺ 900 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የ16 በመቶ ድርሻ አለው።

ኃይል በማመንጨት ላይ የሚገኙት የግድቡ ሁለቱ ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲሆን በግድቡ ላይ የሚተከሉት ቀሪ 11 ዩኒቶች ኃይል ማምረት ሲጀምሩ አሁን በሀገሪቱ ያለውን የማመንጨት አቅም በ83 በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 5,150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖረው ሲሆን ዓመታዊ የኃይል ምርቱም 15 ሺ 760 ጊጋ ዋት ሰዓት ይሆናል።

Scroll to Top