በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢትዮ-ኬኒያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ኮንቨርተር ጣቢያ ምስራቅ አፍሪካን በኃይል ለማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና እየተጨወተ መሆኑ ተገለጸ።
በጣቢያው የጥገናና የኦፕሬሽን ባለሙያ አቶ መኮንን ካሴ እንደተናገሩት የኮንቨርተር ጣቢያው በዲዛይን፣ በቴክኖሎጂ እና በዓይነቱ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው በመሆን በ2014 ዓ.ም ነው ሥራ የጀመረው።
ኮንቨርተር ጣቢያው ከወላይታ ሶዶ ቁጥር ሁለት የማከፋፈያ ጣቢያ በአራት ባለ 400 ኪሎ ቮልት ገቢ መስመሮች ተቀብሎ፣ 12 ኮንቨርተር ትራንስፎርመሮችን እና 1 ሺ 680 ታሪስተሮች(thyristors) ተጠቅሞ ኃይል የሚያስተላልፍ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ጣቢያው 2 ሺ ሜጋ ዋት ኃይል የመሸከም አቅም ባላቸው በሁለት ፖሎች እና ከኢትዮጵያ እስከ ኬኒያ በተዘረጋ 1 ሺ 60 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር አማካይነት ኃይል እያስተላለፍ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከኬኒያ ጋር ባለው የኃይል ሽያጭ ስምምነት መሰረት በአሁኑ ወቅት በቀን 18 ስዓት ማለትም እስከ ምሽት 6 ስዓት ድረስ በሰዓት 200 ሜጋ ዋት እንዲሁም ከዚያ በኋላ በሚኖረው ቀሪ 6 ስዓት ደግሞ በሰዓት 65 ሜጋ ዋት ኃይል እየቀረበ ይገኛል ብለዋል።
ጣቢያው በስምምነቱ መሠረት እየጨመረ የሚሄደውን የኃይል አቅርቦት እና ወደ ታንዛኒያ ኃይል ለማስተላለፍ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል አቅም እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረጉ የኃይል ሽያጭ ስምምነቶችን ተከትሎ አስተማማኝና ኃይል በማስተላለፍ ለአህጉራዊ የኃይል ትስስር መሳለጥ የሚያደርገውን አስተዋጽዖ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ጣቢያው የኃይል ኤክስፖርቱን ለማሳደግ የተያዘውን ጥረት ለመደገፍ ቀጥተኛ ዥረትን (Direct current) የቴክኖሎጅ ዓይነት ወደ ተለዋጭ ዥረት (Alternative Current) ለመለወጥ የተገነባ ማከፋፈያ ጣቢያ በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው አስታውሰዋል።
ቀጥተኛ ዥረት መሆኑ ከ1 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ያለምንም ተጨማሪ ማከፋፈያ ጣቢያ በሁለት መስመር ብቻ ኃይል ለማስተላለፍ ማስቻሉን የተናገሩት ባለሙያው መስመሩ በተለዋጭ ዥረት ዘዴ የተገነባ ቢሆን ኖሮ ምንአልባትም አራት አካባቢ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን መገንባት ያስገድድ ነበር ብለዋል።
በተጨማሪም በፍሪኩየንሲ ልዩነት ምክንያት ግሪድ እንዳይረበሽ፣ የኃይል ብክነት እንዳይኖር፣ ከስምምነት ውጭ ኃይል ከግሪድ እንዳይሄድ እንዲሁም ኃይል መላክ ብቻ ሳይሆን ከኬኒያ ኃይል መቀበል ካስፈለገ ለመቀበል የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።
የኃይል ሽያጩን ላይ መተማመን እንዲኖር ለማድረግም በኮንቨርተር ጣቢያው እና ሱስዋ ናሮክ ግዛት በሚገኘው የኬንያው ኬትራኮ ኮንቨርተር ጣቢያ ላይ የሁለቱ ተቋማት የኢነርጂ ሜትሮች መተከላቸውንም ጠቁመዋል።
ተቋሙ የጣቢያውን የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራውን አስተማማኝ ለማድረግ ወደ 20 የሚደርሱ መሐንዲሶችን ሕንድ አገር ድረስ በመላክ ሥልጠና እንዲወስዱ ማድረጉን የጠቆሙት ባለሞያው ማስተላለፊያ መስመሩ ላይ ችግር እንዳያጋጥም የደቡብ 1 እና 2 ሪጅኖች በሚያዋስኑት አከባቢ መሰረት ተከፋፍለው የጥገና ቡድን በማዋቀር ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



