በጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በራስ አቅም የሚከናወኑ የጥገና ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ሀብታሙ ሰሙ እንደገለጹት ማመንጫ ጣቢያው ሥራ በጀመረበት የመጀመሪያው ዓመት ቻይኖችን በማስገባት የዕውቀት ሽግግር ከተደረገ በኋላ ርክክብ በመፈጸም የጥገና ሥራዎችን በራስ አቅም ማከናወን ጀምሯል።
የኃይል ማመንጫ ጣቢያው 1 ሺ 870 ሜጋ ዋት በማመንጨት ለብሔራዊ የኃይል ቋት ከፍተኛውን ድርሻ የሚያበረክት መሆኑን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ ይኼን ከግምት ያስገባ የቅድመ መከላከል፣ የትንበያ እና የፍተሻ ጥገና ሥራዎች በጣቢያው ባለሙያዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡
በጣቢያው የሚከናወኑ የጥገና ሥራዎችን በራስ አቅም በአግባቡ ለማከናወን ለባለሙያዎቹ አጫጭርና የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡ እና እርስ በእርስ የሚማማሩበት ሥርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል፡፡
ተርባይኖች እንዳይቆሙ የተበላሹ ዕቃዎች ላይ ማሻሽያ በመስራት ጭምር በርካታ የጥገና ሥራዎችን በራስ አቅም የመስራቱ ልምምድ እያደገ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡
ይህም የባለሙያዎችን አቅም በመጠቀም ወጪና ጊዜን በቆጠበ መልኩ አስተማማኝ ኃይል ለማምረት ምቹ መደላድል መፍጠሩን አብራርተዋል።
ከኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ ተቋራጩ የቻይናው ዶንግፋንግ ኤሌክትሪክ ጋር በተደረገ ስምምነት መሰረት የመለዋወጫ ዕቃዎች በወቅቱ እየቀረቡ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ በስምምነቱ ያልተካተቱት ዕቃዎች ደግሞ በግልጽ ጨረታ እየተገዙ ነው ብለዋል።
የጣቢያው የጥገና ባለሙያ አቶ እሸቱ አበራ በበኩላቸው የኃይል ምርቱን በአስተማማኝነት ለመጨመር የሚያስችሉ የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም በጣቢያው የጥገና ወርክሾፕ እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ብሬከሮችን ጨምሮ የማቀዝቀዣ ፓምፖች እና ሌሎች የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
የማቀዝቀዣ ፓምፖች የጥገና ሥራ በውጭ ባለሙያ ቢከናወን ኖሮ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ዕቃዎች ከመጠገን ይልቅ ወደ መቀየር በመግባት ተቋሙን ለተጨማሪ ወጪ ይዳርገው እንደነበር ገልፀዋል።
ዕቃዎቹን በጣቢያው ባለሙያዎች በመስራት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉ ወጪና ጊዜን ከመቆጠቡም በላይ የጣቢያውን የኦፕሬሽን ሥራ የሚያቀላጥፍ ነው ብለዋል።
ሠራተኛው አቅሙን አሟጦ እንዲጠቀም እና ሙያዊ ክህሎቱን በማሳደግ ትልልቅ የጥገና ሥራዎችን መስራት እንችላለን የሚል የራስ መተማመን እንዲኖራቸው ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ እሸቱ የሠራተኛውን አቅም ቀጣይነት ባለው መልኩ የመገንባት፣ የመልዋወጫ እቃ አቅርቦት እና የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጥባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




