የማከፋፈያ ጣቢያው የማስፋፊያ ሥራ 63 በመቶ ደርሷል

የማከፋፈያ ጣቢያው የማስፋፊያ ሥራ 63 በመቶ ደርሷል

የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የወላይታ ሶዶ ሁለተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራ 63 በመቶ መድረሱን ፕሮጀክቱ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የወላይታ ሶዶ ሁለተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሲቪል መሐንዲስ አቶ አበበ ሚጀና እንደገለጹት የእሳት መከላከያ ግድግዳን ጨምሮ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎችን ለማስቀመጥ የሚያግዙ የመሰረት ሥራዎች ተጠናቀዋል።

በአሁኑ ሰዓት የትራንስፎርመር ዘይት የማጣራት ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የፍሳሽ ማስወገጃ እና ገመዶች የሚዘረጉበት ቦይ (ኬብል ትሬንች) ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የአጥር ግንባታ እና መሬቱን ጠጠር የማልበስ ተግባራት ደግሞ በቀጣይ እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

ቀሪ ሥራዎችን ክረምት ከመግባቱ በፊት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

በሥራ ተቋራጩ ሃዮሰንግ ሄቪይ ኢንደስትሪስ ኮርፖሬሽን የማስፋፊያው የሳይት ኢንጂነር አቶ ቁምላቸው ግርማ እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያው የማስፋፊያ ሥራ እያንዳንዳቸው ባለ 250 ሜጋ ቮልት አምፔር የመጫን አቅም ያላቸው ሁለት ባለ400/230 ኪሎ ቮልት ትራንስፎርመሮች ተከላ ሥራን ያካትታል፡፡

ሥራውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ እስከ ህዳር 2018 ዓ.ም ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱ ምዕራፍ አንድ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዷለም መላኩ በበኩላቸው ከ14 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ በጀት የተጀመረው የወላይታ-ሶዶ ሁለተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራ ሲጠናቀቅ ለአርባምንጭ እና ለኦሞ ኩራዝ አካባቢ አስተማማኝ ኃይል ለማስተላለፍ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ 69 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራው ደግሞ 25 በመቶ መድረሱን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ አጠቃላይ አፈጻጸሙ 63 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

ለማስፋፊያ ሥራው አስፈላጊ የሆኑ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች በአብዛኛው ሳይት በመድረሳቸው ሥራውን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የሳይት ሥራ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top