ጣቢያው ለበጀት ዓመቱ የሚያገለግል በቂ የውሃ መጠን በግድቡ ይዟል

ጣቢያው ለበጀት ዓመቱ የሚያገለግል በቂ የውሃ መጠን በግድቡ ይዟል

የጊቤ 3 የውha ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ2017 በጀት ዓመት ኃይል ለማመንጨት የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል የውሃ መጠን በግድቡ መያዙን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ሀብታሙ ሰሙ እንደገለጹት ጣቢያው በ2016 በጀት ዓመት ከፍተኛ ኃይል ለማመንጨት ሲባል እና በግድቡ ላይ ይሰሩ በነበሩ የጥገና ሥራዎች ምክንያት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ወራት በግድቡ የነበረው የውሃ መጠን ከሌሎቹ ዓመታት በተለየ ዝቅ ያለ ነበር፡፡

በግድቡ የነበረው የውሃ መጠን ከባህር ጠለል በላይ ወደ 832 ሜትር ዝቅ በማለቱ ጣቢያው በክረምቱ ወራት ወደ ግድቡ ይገባ የነበረውን ውሃ ማጠራቀም ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲስራ መቆየቱን አንስተዋል።

አሁን ላይ በግድቡ ያለው የውሃ መጠን ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ወደ 881 ነጥብ 6 ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

ሥራ አስኪያጁ እንደገለፁት ጣቢያው ከክረምቱ መግቢያ በፊት በ2017 በጀት ዓመት 5 ሺ 400 ጊጋ ዋት ስዓት ኃይል ለማመንጨት አቅዶ ነበረ፡፡

ይሁንና ክረምቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ግድብ የገባው ውሃ ከተገመተው ከፍ ያለ በመሆኑ በክረምት የገባውን የውሃ መጠን ታሳቢ በማድረግ 6 ሺ 165 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማመንጨት የእቅድ ክለሳ መደረጉንም ገልፀዋል።

አሁን በግድቡ ያለው የውሃ መጠን ጣቢያው በቀሪ በጀት ዓመት ያለምንም የውሃ እጥረት ኃይል የማመንጨት ተግባሩን በአስተማማኝነት እንዲያከናውን ለማድረግ የሚያስችለው መሆኑን አቶ ሀብታሙ ገልጸዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ እቅዱን ለማሳካት ከውሃ አስተዳደር ሥራው ጎን ለጎን ሣምንታዊና ወርሃዊ የጥገና ሥራዎች በዕቅድ ተይዘው በመከናወን ላይ ናቸው።

በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ጣቢያው በዋናነት በግድቡ ውሃ ማጠራቀም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ የነበረ ቢሆንም ግሪዱ ላይ በነበረው ፍላጎት ምክንያት የእቅዱን 141 በመቶ ኃይል ማምረት መቻሉን አስታውቀዋል።

ታኅሣሥ 8 ቀን 2009 ዓ.ም ተመርቆ ሥራ የጀመረው የጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአስር ተርባይን 1 ሺ 870 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠ https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ – ገፃችንንም ይጎብኙ www.eep.com.et
ታህሳስ 04 ቀን 2017 ዓ.ም

Scroll to Top