የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በከተማው የሚገኘውን ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ይዞታ የማስከበር ሥራ እንደሚሰራ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ገለፁ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ጋር በኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሃ ጌታቸው ለከንቲባው እንደገለፁት ተቋሙ በኃይል ማመንጨት እና ማስተላለፍ ዘርፍ ለሀገር ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
ሁለቱ ኃይል አቅራቢ ተቋማት በስያሜ ደረጃ የተለያዩ ቢሆኑም ለህብረተሰቡ ኤሌክትሪክ ተደራሽ በማድረግ በኩል ኃላፊነታቸውን በጋራ እየተወጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
እንደ አቶ ፍስሃ ገለፃ በደብረ ብርሃን ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ታሳቢ ያደረጉ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡና አቅማቸው እያደገ ይገኛል።
ከተማ አስተዳደሩ ከደብረ ብርሃን ቁጥር ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ጋር ተያይዘው ለሚስተዋሉ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ነው የጠየቁት።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደብረ ብርሃን ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ በበኩላቸው እንደተናገሩት ለህብረተሰቡ የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ከዞኑ እና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው።
ከኃይል መቆራረጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ የወሰን ማስከበር እና ዛፎችን የማፅዳት ሥራዎችን ከወረዳና ቀበሌዎች ጋር በትብብር እንዲሰራም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ከተማዋ የተሻለ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖራት ተቋማቱ ላከናወኗቸው የልማት ሥራዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በከተማዋ ማስተር ፕላን ውስጥ ለአራት አዳዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ የሚያገለግሉ ቦታዎች መካተታቸውን የጠቀሱት ከንቲባው ካሳ የተከፈለባቸው የኃይል መሰረተ ልማቶችን በማስጠበቅ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኙ እናደርጋለን ብለዋል።
እንደ ከንቲባው ገለፃ ከተማ አስተዳደሩ በአካባቢው ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ያማከለ ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት እየጠየቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ደህንነት መጠበቅ ግዴታው ነው።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የኃይል አቅራቢ ተቋማቱ በከተማዋ ለሚያከናውኗቸው የልማት ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አቶ በድሉ አረጋግጠዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



