የደብረ ብርሃን ቁጥር ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ለከተማዋ እና በዙሪያዋ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ ኃይል በማቅረብ ቁልፍ ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለፁ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ዳኜ ይታገሱ እንደገለፁት ጣቢያው የደብረ ብርሃን ከተማን የኃይል አቅርቦት ችግርና በአካባቢው ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ የተገነባ ነው።
በመሆኑም የደብረ ብርሃን ከተማን ጨምሮ የወረዳ ከተሞችን እንዲሁም የኢንዱስትሪዎችን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ በመመለስ የአካባቢው የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲሻሻል ማድረጉን ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ቁጥር ሁለት የማከፋፈያ ጣቢያ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው ሁለት ባለ 125 እና ሁለት ባለ 63 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች እንዳሉት አቶ ዳኜ ጠቁመዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው በቀጥታ ለኢንዱስትሪዎች እና ለህብረተሰቡ ኤሌክትሪክ የሚያቀርቡ ዘጠኝ ባለ 33 እና አስር ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት።
በ33 ኪሎ ቮልት ለደብረ ብርሃን፣ እነዋሪ፣ ጅሁር፣ ሸኖ፣ ሀገረ ማሪያም እና ጊናገር ከተሞች እንዲሁም ለደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ለብቅል፣ ለብርጭቆ፣ ለብረት ድስት፣ ለእብነ በረድ ፋብሪካዎች ኃይል እያቀረበ ነው ብለዋል።
ጣቢያው አገልግሎት መስጠት በጀመረበት ወቅት ከ2 ሜጋ ዋት ያልበለጠ ኃይል ያቀርብ እንደነበር ያወሱት ሥራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅት በአንድ ወጪ መስመር ብቻ ከ15 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት በ33 ኪሎ ቮልት 25 ሜጋ ዋት እንዲሁም በ15 ኪሎ ቮልት 48 ሜጋ ዋት ኃይል እያቀረበ ይገኛል ያሉት አቶ ዳኜ ከጣቢያው ኃይል እያገኙ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ አሁን ካለው ከፍ እንደሚልም ነው የጠቆሙት።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው በዳታ ማይኒንግ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ለሦስት የቻይና ኩባንያዎች 30 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት ኃይል እያቀረበ ነውም ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ቁጥር ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በአካባቢው መገንባቱ ለዞኑ እና ለከተማው መልካም አጋጣሚ መፍጠር ችሏል ያሉት አቶ ዳኜ ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን አወንታዊ ሚና መጫወቱንም ገልፀዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአካባቢው ያለው የኢንቨስትመንት ቁጥር መጨመር ጣቢያው በየዓመቱ ከ50 ሜጋ ዋት በላይ የኃይል አቅርቦት ዕድገት እንዲያሳይ አድርጓል።
በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ፈጣን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ታሳቢ የሚያደርጉ ተጨማሪ ወጪ መስመሮች መገንባት እንደሚኖርባቸውም ነው የጠቆሙት።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





