የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ከ620 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው

የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ከ620 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው

ከ620 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር በቀጣዩ የፈረንጆች 2025 በይፋ ሥራ ሊጀምር ነው።

በኬንያ መንግሥት፣ በምስራቅ አፍሪካ ፓወር ፑል እና በዓለም ባንክ አዘጋጅነት የፑሉ አባል ሀገራት ከፍተኛ የሚኒስትሮች ጉባዔ በኬንያ የወደብ ከተማ ሞምባሳ ተካሒዷል።

የምስራቅ አፍሪካ ፓወር ፑል ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚገኘውን ኢነርጂ በአነስተኛ ዋጋ ቀጣይነት ባለው መልኩ በሁሉም አባል ሀገራት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጿል።

የምስራቅ አፍሪካ የኢነርጂ ሚኒስትሮች ቀጣናዊ የኃይል ሽያጭን ለማሳደግ ገበያ ተኮር አሰራርን መዘርጋት፣ በኃይል ትስስር ፍኖተ ካርታ እንዲሁም የተሻለ ልምድና ተሞክሮ ከመሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት መውሰድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አካሒደዋል።

የተዘረጉ የኃይል መሰረተ ልማቶችን በጋራ የመጠቀምና ተወዳዳሪ የኃይል ሽያጭ ሥርዓትን የማስፈን እንዲሁም ለቀጣናዊ የጋራ ግቦችና ዘላቂ ልማት በትብብር መስራት ሚኒስትሮቹ ከመከሩባቸው አበይት ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

በጉባዔው እንደተገለፀው በቀጣናው የሚፈጠረው የኃይል ትስስር ለዜጎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማዳረስ የሚያስችል ነው ተብሏል።

በፈረንጆቹ 2025 በይፋ ሊጀመር የታሰበው የኃይል ትስስር ለሀገራቱ ዕድገት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የተገለፀ ሲሆን ዕቅዱ በቀጣናው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር በማስቻል ኢኮኖሚያዊ ምርታማነትን እንደሚያሳድግ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

በጉባዔው የኬንያ የኢነርጂ እና ነዳጅ ሚኒስቴር ካቢኔ ፀሐፊ ጄምስ ኦፒዮ ዋንዳይ እንደተናገሩት እንደ ፖሊሲ አውጪ አካል በአባል ሀገራቱ መካከል ለሚፈጠረው የኃይል ሽያጭ ገቢያ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ግዴታችን ነው።

እንደ ፀሐፊው ገለፃ የትብብር ባህልን ማጎልበት፣ በቁጥጥር እና ቴክኒክ ማዕቀፎች ላይ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን የመፍታት እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ሀገራዊ ጉዳዮች ከቀጣናዊ ግቦች ጋር እንዲጣጣሙ የማድረግ ሥራ መስራት ያስፈልጋል።

በአሁኑ ወቅት አባል ሀገራቱ በቀጣናው የኃይል ሽያጭ ገበያን ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ተቋማዊ ማዕቀፎችን ለማዘጋጀት እና መድረኮችን ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ፓወር ፑል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበር ሚስተር ኦሳካይ ኦፖሎት በበኩላቸው ቀጣናዊ እና ሀገራዊ የኢነርጂ ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን ማዋሃድ አባል ሀገራቱ ወደ አንድ የገበያ መር ማዕቀፍ ለሚያደርጉት ሽግግር እንዲሁም የታዳሽ ኃይል ልማትን በማፋጠን የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማሳደግ ላላቸው ራዕይ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ለኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ላይ ስትሆን፣ ኬንያ በበኩሏ ኢትዮጵያን ከታንዛኒያ ጋር የሚያስተሳስረውን ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ በቅርቡ ማጠናቀቋ ይታወቃል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top