የሰመራ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን የኦፕሬሽንና ቁጥጥር ስርዓት ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ጣቢያው አስታወቀ፡፡
የጣቢያው ኃላፊ አቶ ኢንድሪስ አህመድ እንዳስታወቁት የማከፋፈያ ጣቢያውን የቁጥጥር ስርዓት ጂ.አይ.ኤስ በተሰኘ ዘመናዊ መቆጣጠሪያ ብሬከር ለመቀየር የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የጂ.አይ.ኤስ ፓናሎችን ወደ ጣቢያው የማጓጓዝ እና ሥራው እስኪጠናቀቅ ጊዜያዊ አገልግሎት የሚሰጠው የተንቀሳቃሽ ስዊች ጊር የሚቀመጥበትን ቦታ የመምረጥና የመግቢያ መንገዶችን የማስተካከል ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።
በማዘመን ሥራው በጣቢያው ባለ33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ላይ ስድስት ብሬከሮች እንደሚተከሉም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ኢንድሪስ ገለፃ የመቆጣጠሪያ ብሬከር የማዘመን ሥራው የኃይል ብክነትን ለመቀነስ፣ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን ለማቀላጠፍ፣ የኃይል መቋረጥ ጊዜን ለማሳጠርና ለማስቀረት፣ ከኃይል መቆራረጥ ጋር በተያያዘ በደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቀነስ እንዲሁም የጣቢያው ሠራተኞችን ጊዜ እና ጉልበት ለመቆጠብ ይረዳል፡፡
የሚቀየሩ ብሬከሮቹ ለረጅም ዓመታት የሚያገለግሉ በመሆናቸው ተቋሙ ለጥገናና ሥራ እና ለተጨማሪ ብሬከር ግዥ የሚያወጣውን ወጪ እንደሚቀንስ የጣቢያው ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
ሥራው ኃይል ሳይቋረጥ ጊዜያዊ የተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ በማስቀመጥ እንደሚከናወንም ነው የገለፁት።
በተቋሙ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ማስተባበሪያ አንድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ጌታሁን በበኩላቸው የብሬከር ቅየራው በአካባቢው አስተማማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡
የብሬከር ማዘመኑ የኃይል መቋረጥን በመቀነስ ተቋሙ ከኃይል ሽያጭ የሚያገኘውን ገቢ ያሳድገዋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሥራው እስኪጠናቀቅ ጊዜያዊ አገልግሎት የሚሰጥ የተንቀሳቃሽ ሲዊች ጊር ወደ ቦታው ለማጓጓዝ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ እንደሆነና የቅየራ ሥራውን ከሁለት ሳምንት በኋላ ለመጀመር መታቀዱንም ነው ሥራ አስኪያጁ የገለፁት፡፡
የብሬከር ቅየራ ሥራው በሰሜን ምስራቅ 2 ሪጅን የጥገና ሠራተኞች እና ከሪጅን ማስተባበሪያ ቢሮ በተውጣጡ ባለሙያዎች እንደሚከናወን የተናገሩት አቶ ፀጋዬ በራስ አቅም መከናወኑ ተቋሙ ለውጭ ባለሙያዎች የሚያወጣውን ወጪ ያስቀራል ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት በተለያዩ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ተመሳሳይ ሥራዎች በራስ አቅም መከናወናቸውን እና ከዚህም ለቀጣይ ሥራዎች ግብዓት የሚሆን ልምድና የዕውቀት ሽግግር እንደተገኘበት አስታውሰዋል፡፡
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የሰመራ ማከፋፈያ ጣቢያ 25 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያለው አንድ ትራንስፎርመር፣ አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ፣ ስድስት ባለ 33 እና ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



