የሐዋሳ ቁጥር 2 ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ በአካባቢው ለሚገኙ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች፣ ለቴክኖሎጂ ድርጅቶች እና ለማህበረሰቡ ከ200 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ የጣቢያው ኃላፊ ገለፁ።
ኃላፊው አቶ ዳንኤል አንጄሎ እንደገለፁት በ2011 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የማከፋፈያ ጣቢያው እያንዳንዳቸው 125 ሜጋ ቮልት አምፔር ኃይል የመሸከም አቅም ያላቸው ሁለት አውቶ ትራንስፎርመሮች እና ሁለት ፓወር ትራንስፎርመሮች አሉት፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው 28 ሜጋ ዋት ለከተማው ነዋሪዎች፣ 40 ሜጋ ዋት ለኢንዱስትሪዎች እንዲሁም 135 ሜጋ ዋት ለቴክኖሎጂ ተቋማት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


በጣቢያው ከሚገኙ 28 ወጪ መስመሮች መካከል ስድስት የባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ለሀዋሳ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች፣ 18 የባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች በቀጥታ መስመር (dedicated line) በአካባቢው ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች እንዲሁም ለቴክኖሎጂ ድርጅቶች ኃይል እያቀረቡ ሲሆን አራቱ ደንበኛ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
አቶ ዳንኤል እንዳሉት የኃይል ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን ተከትሎ ቀጥታ በተዘረጉ የባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ከሦስት ዓመት በፊት ጥቅም ላይ ይውል የነበረው 20 ሜጋ ዋት አሁን ላይ እስከ 200 ሜጋ ዋት ደርሷል።
በተጨማሪም ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የነበሩ 2 የባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ወደ 8 እንዲሁም የባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭዎቹ ከ 2 ወደ 6 ከፍ ማለታቸውን አብራርተዋል።

ይህም ጣቢያው ለኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች በቂና አስተማማኝ ኃይል በተገቢው ሁኔታ በማቅረብ ዓላማውን እያሳከ እንደሚገኝ አመላካች ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ዳንኤል ገለፃ ማከፋፈያ ጣቢያው የነባር ደንበኞቹን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ እያደገ ለሚመጣው የኢንዱስትሪ ልማት የሚያስፈልገውን ኃይል ለማሟላት የተጠናከረ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

