በኦሞ ጊቤ ተፋሰስ ላይ የተገነቡት የግልገል ጊቤ 1 እና 2 እንዲሁም የጊቤ 3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በአግባቡ መጠቀም የመጀመሯ ማሳያ መሆናቸውን የአፍሪካ አመራረረ ሥራ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ይህ የግቤ ሰንሰለት የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልና የኢኮኖሚ ከፍታ ማሳያ ከመሆኑም በተጨማሪ የቀጠናው የኃይል ማማ እንድትሆን አስችሏታል።
እ.ኤ.አ በ2004 ሥራ የጀመረው የግልገል ግቤ 1፣ 184 ሜጋ ዋት በማመንጨት በወቅቱ የነበረውን የኃይል እጥረት በመቅረፍ ለሀገሪቱ የኢንዱስትሪ መነሳሳት መሠረት እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህ ግንባር ቀደም ፕሮጀክት የኦሞ ወንዝን ያልተገራ ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ ለታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ያዋለ ታሪካዊ ስኬት መሆኑንም አብራርተዋል።
እንደ አቶ ዛዲግ ገለጻ የዘመኑን የኢንጅነሪንግ ቴክኒዮሎጅ የተገለጠበት የግልገል ጊቤ 2 ማመንጫ ትልቅ የውኃ ማጠራቀሚያ ሳይኖረው ከግልገል ግቤ 1 የወጣውን ውኃ በ26 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው የተራራ ውስጥ ዋሻ አሳልፎ ቁልቁል በመጣል 420 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል።

ተጨማሪ ወንዝ ሳይገደብ በአንድ ወንዝ ላይ የተሠራውን ውሃ በድጋሚ በመጠቀም ኃይል ማመንጨቱ የኢትዮጵያ ምሁራንና መሐንዲሶች ያሳዩት የብልሃትና የጥበብ ሥራ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀጥሎ የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረው ግዙፉ ግቤ 3 ደግሞ 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ግድቡ ሥራ በጀመረበት ወቅት የሀገሪቱን አጠቃላይ የኃይል አቅርቦት በአንድ ጊዜ በእጥፍ ማሳደጉን ያወሱት ፕሬዝዳንቱ ግድቡ በግንባታው ወቅት በ243 ሜትር በአፍሪካ ረጅሙ ግድብ ተብሎ መመዝገቡ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ለኬንያ፣ ለጂቡቲ እና ለሱዳን የሚሸጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ዋነኛው ምንጭ ግቤ 3 በመሆኑ ለሀገሪቱ በየዓመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛልም ብለዋል።
ሦስቱ ኃይል ማመንጫዎች ውኃን በቁጠባና በከፍተኛ ብቃት ለመጠቀም የሚያስችል ሥርዓት በኢትዮጵያ ያስተዋወቁ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የኦሞ ወንዝ በየዓመቱ የሚያደርሰውን የጎርፍ አደጋ በመቀነስ የታችኛው የኦሞ ሸለቆ ነዋሪዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲኖሩና በመስኖ ልማት እንዲሰማሩ ዕድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል።
በቀጣይ ጊዜ ግቤ 4 እና ግቤ 5 ሲገነቡ የኦሞ ወንዝ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ዋስትና መሆኑ የማይካድ ሃቅ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የግቤ የግድቦች ሰንሰለት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በቴክኖሎጂ ታግዛ ወደ ብርሃን፣ ወደ ኢንዱስትሪና ወደ ኢኮኖሚ ከፍታ የለወጠችበት የታላቅነት ምስክር ነው መሆኑንም አብራርተዋል።
እያንዳንዱ ሜጋ ዋት ለኢንዱስትሪ ዕድገት አዲስ ተስፋ የሚሰጥ ሲሆን ውኃ የኢትዮጵያ ነዳጅ መሆኑን በተግባር ያረጋገጡ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አቶ ዛዲግ አስገንዝበዋል።