በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት የተቋሙን ተሽከርካሪዎች በራስ አቅም በመጠገን ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተሽከርካሪ ጥገና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ብሩክ እንዳለ እንደገለጹት ቢሮው በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት በተቋሙ ጋራዥ ለ1 ሺህ 227 ተሽከርካሪዎች የቀላል፣ መካከለኛ እና ከባድ የጥገና ሥራዎች አከናውኗል፡፡
በተቋሙ ጋራዥ በራስ አቅም ጥገናዎችን ማከናወኑ ተሽከርካሪዎች በጥገና የሚቆዩበትን ጊዜ በማሳጠር፣ የተሽከርካሪዎችን የጥገና ታሪክ በቀላሉ በመመዝገብ እና በመከታተል የተሽከርካሪዎችን ዝግጁነት ማሳደጉን የገለጹት አቶ ብሩክ በተከናወነው ጥገናም 31 ነጥብ 58 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ተናግረዋል፡፡


የተሽከርካሪዎች ጥገና የተጀመረበትን እና የሚጠናቀቅበትን ጊዜ በመመዝገብ እና ክትትል በማድረግ እንዲሁም የመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦቱን በማሻሻል የጥገና ሥራዎች በጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በተሰራው የጥገና ሥራ ችግሮች መቀረፋቸውን ለማረጋገጥ የመሣሪያ እና የክፍሎች ምርመራ የማከናወን፣ የተቀየሩ የመለዋወጫ ዕቃዎች በትክክል መገጠማቸውን የማረጋገጥ እና የደህንነት ምርመራ በማድረግ ወደ አገልግሎት የማስገባት ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
በተቋሙ ጋራዥ የመለዋወጫ ዕቃዎች በማይኖሩበት ጊዜ በአስቸኳይ ግዥ እንዲሟላ በማድረግ የጥገና ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የጠቆሙት አቶ ብሩክ የመለዋወጫ እቃዎች ግዥ እና ክምችት ላይ ብክነት እንዳይኖር በየጊዜው የክትትል ቁጥጥር ሥራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።

