የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ለማሻሻል የሚያስችል የኢነርጂ ትግበራ ሞዴል ለማዘጋጀት እየተሰራ ነው

የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ለማሻሻል የሚያስችል የኢነርጂ ትግበራ ሞዴል ለማዘጋጀት እየተሰራ ነው

የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ለማሻሻል የሚያስችል የኢነርጂ ትግበራ ሞዴል ለማዘጋጀት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

ተቋሙ ከዴንማርክ የኢነርጂ ኤጀንሲ እና ኢነርጂኔት የኤሌክትሪክ ኃይልና የጋዝ አቅርቦት ኩባንያ ጋር በመተባበር በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉ መዘግየቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

አውደ ጥናቱ በዴንማርክ – ኢትዮጵያ የኢነርጂ ትብብር (Danish-Ethiopian Energy Partnership) ማዕቀፍ ስር የተዘጋጀ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ መሪዎች እና ባለሙያዎች ከፕሮጀክት ትግበራ ሞዴል ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን እንዲቀስሙ ያለመ ነው።

በመርሀ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ተወካይ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ያለውአይቀር ማንደፍሮ እንደገለፁት በተቋሙ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የፕሮጀክት ትግበራ ሞዴል ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡

ኢነርጂኔት የተሰኘው ኩባንያ ከኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ጋር ተያይዞ ያለውን የካበተ ልምድ ለተቋሙ ባለሙያዎች ማካፈሉ ተቋሙ የራሱን የፕሮጀክት ትግበራ ሞዴል ለማዘጋጀት ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት በኮይሻ፣ በአሰላ፣ በአይሻ  2፣ በደቡብ ግሪድ እና በበቆጂ ፕሮጀክቶች ላይ ጥናቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውንና የጥናቱ የመጀመሪያ ውጤት ለተቋሙ ከፍተኛ የሥራ አመራር እንዲቀርብ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

በኢነርጂኔት የኤሌክትሪክ ኃይልና የጋዝ አቅርቦት ኩባንያ የፕሮጀክት ሞዴልና ቱልስ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሚኬል ኔልሰን የሌሎች ሀገራትን የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታ አፈፃፀም ተሞክሮዎችን እንደ መነሻ መጠቀም ጥሩ ቢሆንም ሞዴሎቹን ከሀገር በቀል እና ከተቋም ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ማጣጣም የግድ እንደሚል አሳስበዋል።

በዴንማርክ የአካባቢ ጥበቃ ፈቃድ፣ የትራንስፎርመር እና ኮንዳክተር ሽቦ ግዥ ዋነኛ የፕሮጀክት ግንባታ ማነቆዎች ናቸው ያሉት ሥራ አስኪያጁ በኢትዮጵያ ከኃይል መሠረተ ልማት ግንባታ አፈፃፀም ጋር ተያይዘው የሚነሱ ተግዳሮቶችን መለየት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

የዴንማርክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ልዩ አማካሪ አቶ ደረጄ ፈንቴ በበኩላቸው አውደ ጥናቱ ቀደም ሲል ከተቋሙ ጋር በጋራ በተከናወኑ ሥራዎች ላይ የታዩ ተግዳሮቶችን መነሻ በማድረግ የቀረበ የመፍትሄ አካል መሆኑን ገልፀዋል።

ኤጀንሲው የተቋሙ አጋር በመሆን የቴክኒክ ድጋፎችን በመስጠት እና በማመቻቸት የኢትዮጵያን የኢነርጂ ዘርፍ ለማገዝ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

እንደ አቶ ደረጄ ገለፃ ጥናቱ በፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት የሚባክኑ የፋይናንስና የጊዜ ሀብቶችን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ዮሴፍ ፕሮጀክቶች ሲታቀዱ ተጨባጭ የሆነ የጊዜ ገደብ አለማስቀመጥ፤ በአዋጭነት ጥናት ወቅት ሁሉንም ጉዳዮች ያካተተ ጥናት አለማካሄድ፤ ከማህበረሰቡ ጋር የሚደረግ የግንኙነት እና የውይይት ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል፡፡

Scroll to Top