ተቋሙ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለአካባቢው የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ  ሰጥቷል

ተቋሙ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለአካባቢው የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ  ሰጥቷል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በወላይታ ሶዶ ኮንቨርተር ጣቢያ ዙሪያ ለሚገኙ ነዋሪዎች የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ መስጠቱን በተቋሙ የወላይታ ሶዶ ኮንቨርተር ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ሀብታሙ ግርማ እንደገለፁት ተቋሙ በሶዶ ከተማ የሚገኙ 12 ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሰራው ሥራ የአካባቢው ነዋሪዎችን እርካታ አሳድጓል፡፡

ቀበሌዎቹን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከተመደበው ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ውስጥ 60 በመቶውን ወይም 150 ሚሊዮን ብሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሲሸፍን የተቀረውን 40 በመቶ ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሸፈኑን ገልፀዋል፡፡

የተከናወነው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ሲደርሱ የነበሩ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከሆኑት ቀበሌዎች መካከል በሶዶ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ የዋጃ ቄሮ እና የወረዛ ላሾ ቀበሌ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ሁለቱ ተቋማት ለአካባቢው የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ በመስጠታቸው አመስግነዋል፡፡

አቶ አብነት ይገዙ እና መምህርትተስፋነሽ ወልዴ የተባሉ የዋጃ ቄሮ ቀበሌ ነዋሪዎች እንደተናገሩት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ የእህል ወፍጮን ጨምሮ ከዚህ በፊት ረጅም ርቀት በመጓዝ ሲያገኙት የነበረውን የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በቅርበት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡

በተጨማሪም የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን የሚያቃልሉ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤዎችን እንዲከተሉና ከቴክኖሎጅ ጋር እንዲተዋወቁ በማድረግ ከዚህ በፊት ይደርስባቸው የነበሩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን እንዳቃለለላቸውም ተናግረዋል።

አቶ ኢሳያስ ገ/ሚካኤል እና አቶ መንግስቱ ንጋቱ የተባሉ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማሩት የወረዛ ላሾ ቀበሌ ነዋሪዎች በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባለፈ አሰራራቸውን በዘመናዊ መንገድ እንዲያከናውኑ በማገዝ ከአላስፈላጊ ወጪዎች መታደጉንና የደንበኞቻቸውን እርካታ በማሳደግ በኩልም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

የዋጃ ቄሮ ቀበሌ ነዋሪ የሆነችው ተማሪ ሊዲያ ቡንዳንሳ በበኩሏ አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ከመሆኑ በፊት በኩራዝ ታጠና እንደነበር በማስታወስ ይህም በውጤቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮባት እንደነበር ተናግራለች።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ አሁን ላይ በትምህርቷ ውጤታማና ከሌሎች ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን እንዳስቻላትም ነው የገለፀችው። ነዋሪዎቹ ሁለቱ ተቋማቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ያደረጉትን ድጋፍ በመገንዘብ የኃይል መሠረተ ልማቶችን በኃላፊነት ስሜት እንደሚጠብቁ አረጋግጠዋል።

Scroll to Top