በስርቆት ምክንያት ኃይል የተቋረጠበት የይርጋለም ቁጥር 2 – ሐዋሳ ቁጥር 2 ባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥምር የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዳግም ወደ አገልግሎት መመለሱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ 1 ሪጅን አስታወቀ፡፡
በሪጂኑ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞሲሳ ገልቻ እንደገለፁት በማስተላለፊያ መስመሩ ላይ በተፈፀመበት ስርቆት ምክንያት አንድ የኃይል ማተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶ በመውደቁ ከመጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ መስመሩ ኃይል ማስተላለፍ አቋርጧል፡፡
የወደቀውን ባለ 230 ኪሎ ቮልት የብረት ምሰሶ በጊዜያዊነት በባለ 132 ኪሎ ቮልት የብረት ምሰሶ በመተካት ተቋርጦ የነበረው መስመር ዳግም ወደ አገልግሎት መመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በመስመሩ መቋረጥ ምክንያት በከፊል ኃይል ሲያገኙ የነበሩ ደንበኞች ሙሉ በሙሉ እንዲያገኙ መደረጉን በመግለጽ ኃይል በከፊል ተቋረጦ በነበረበት ወቅት በትዕግስት ለጠበቁ ደንበኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የወደቀውን ምሰሶውን ወደነበረበት በመመለስ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ሞሲሳ ገልፀዋል፡፡

