ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ለሐዋሳ ከተማ ዕድገት አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው

ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ለሐዋሳ ከተማ ዕድገት አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው

በሐዋሳ ከተማ የሚገኙት ሁለቱ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለከተማዋ ሁሉን አቀፍ ዕድገት ከፍተኛ  አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

በከተማዋ መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት መምሪያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበራ አዴላ እንደገለፁት በከተማው ያለው የኃይል አቅርቦት ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው።

የኃይል አቅርቦቱ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ከሚኖረው ሚና ባለፈ ለከተማ ውበት፣ የማህበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚኖረው ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል።

በከተማው የሚገኙት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለኢንቨስትመንት መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረጋቸው በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት፣ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን እና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች 942 ኢንቨስትመንቶች ወደ ሥራ መግባታቸውንም ኃላፊው ጠቅሰዋል።

ለኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚቀርቡ የኃይል ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ያነሱት አቶ አበራ ወደ ፊት ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በሚከናወነው ሥራ ከተማ አስተዳደሩ ከሚተማመንባቸው ዘርፎች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዋነኛው እንደሆነም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በከተማዋ የሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኢንቨስትመንትን የበለጠ በማነቃቃት ለከተማዋ ሁሉን አቀፍና ፈጣን ዕድገት የላቀ አበርክቶ እያደረጉ እንደሆነም  ጠቁመዋል።

ጣቢያዎቹ ሐዋሳ ከተማ አሁን ለደረሰችበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሠረት መሆናቸውን ተናግረው በከተማዋ ያለውን አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ታሳቢ በማድረግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ለከተማ አስተዳደሩ እየቀረቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የታቦር ፎም ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ኃይለማርያም በበኩላቸው በአካባቢው የሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች  የኃይል አቅርቦት አስተማማኝ እንዲሆን በማድረግ ምርታማነት እንዲጨምርና ምርቶቻቸውን ለደንበኞች በአግባቡና በተፈለገ ጊዜ ለማቅረብ ዕድል ፈጥሮላቸዋል ብለዋል ።

በአካባቢው ያለውን የኃይል አቅርበት ዋስትና በማድረግ በፋብሪካው ላይ ተጨማሪ ማሽኖችን በመትከል የማስፋፊያ ሥራዎችን ለማከናወን እና ሌሎች ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም እየተሠራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

Scroll to Top