ለተከበራችሁ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ፤

ለተከበራችሁ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ፤

እንኳን ለ1447ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ።

ረመዳን የራስን ፍላጎት በመግታት ለላቀ ዓላማ የመገዛት፣ የመረዳዳትና የጽናት ወር ነው። ይህ መንፈስ ደግሞ እኛ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ለምንከተለው “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!” ለሚለው ተልዕኳችን ዋነኛ ስንቅ ነው።

ተቋማችን በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ የተመሰረቱ ግዙፍ የኃይል ማመንጫዎችን፣ የማከፋፈያ ጣቢያዎችንና የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በመገንባት የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ቀን ከሌሊት እየደከመ ይገኛል። ይህ ጉዞ ያለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ፣ እንዲሁም ያለ ተቋማችን ሠራተኞች ጥረት፣ መስዋዕትነትና ብርቱ ተጋድሎ ሊሳካ የሚችል እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡

በመሆኑም ዛሬም እንደ ትናንቱ፣ በብርሃን ጉዟችን ላይ የሚገጥሙንን ፈተናዎች በጋራ በማለፍ፣ ለሀገራችን የኢንዱስትሪና የማኅበራዊ እድገት የጀርባ አጥንት የሆነውን ኃይል ለማቅረብ ሁላችንም በጋራ እንድንተጋ ጥሪዬን አቀርባለሁ። በተመደባችሁበት ፈታኝ የሥራ ሁኔታ እና ቦታ ውስጥ የምትከፍሉት ዋጋ ለሚሊዮኖች ተስፋ የሚሰጥ የሀገር ኩራት እንደሆነ አምናለሁ።

ታላቁ የኢድ አል-ፈጥር በዓል የሠላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሁም አንድነታችን ይበልጥ የሚጠነክርበት እንዲሆን ከልብ እመኛለሁ።

ኢድ ሙባረክ!

አሸብር ባልቻ(ኢንጂነር)
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ

Scroll to Top