የሴቶችን የአመራርነትና እና ውሳኔ ሰጪነት ሚና በማሳደግ ሴቶች በዘርፉ ላይ የላቀ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል በትኩረት እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መመሪያ አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከ60 በላይ ለሚሆኑ የተቋሙ ሴት አመራሮች በሁለት ዙር ሲሰጥ የቆየው የአመራርነት ሥልጠና ተጠናቋል፡፡
በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የመምሪያው ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ እንደገለጹት የተቋሙ ሴት አመራሮች ሥራዎችን በብቃት ቢያከናውኑም ራሳቸውን ወደ ፊት በማምጣት እና ሥራዎቻቸውን በማሳየት ረገድ ግን ውስንነቶች አሉባቸው፡፡

ሥልጠናው የአቅም ግንባታ፣ መታየት (visibility)፣ ራስን በግልፅ ማስተዋወቅ እና መናገር በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ እና በጥናት የተለዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡



እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ የተሰጠው ሥልጠና ሴቶች በተለያዩ መድረኮች በመሳተፍ፣ በመጠየቅ እና ሀሳባቸውን በመግለፅ መታየት እንዲችሉ እና አቅማቸውን እንዲያስተዋውቁ በማስቻል ከራሳቸው አልፎ በሥራቸው ያሉ ሴቶችን በማብቃት ወደ አመራርነት እንዲመጡ ያግዛል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው የተሰጠው ሥልጠና ክፍተቶቻቸውን ለመሙላት እና ራሳቸውን ለማየት የሚያስችል ልምድ የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡



