ሪጅኑ ለሚቀርቡለት የኃይል ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ እየሰጠ ነው

ሪጅኑ ለሚቀርቡለት የኃይል ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ እየሰጠ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ 2 ሪጅን ከደንበኞች ለሚቀርቡለት የኤሌክትሪክ ኃይል ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ታዬ ተናገሩ።

አቶ ምትኩ እንደተናገሩት አሁን ላይ በሪጅኑ የሚቀርቡ የኃይል ፍላጎት ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ የሚያስችል በቂ ኃይል በመኖሩ ከደንበኞች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል።

ይሁንና ከኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ከከተሞች ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ እየጨመረ የሚመጣው የኃይል ፍላጎት ጥያቄ በአግባቡ ለማስተናገድ ከወዲሁ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ሪጅኑ ለኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በመለየት በጣቢያዎች ላይ የማስፋፊያ፣ የሲዊች ጊር ማዘመንና ማሻሻል ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በሶዶ ቁጥር 1፣ ሆሳዕና፣ ቀይ አፈር እና ሳውላ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የተከናወነውንና በመከናወን ላይ የሚገኘውን የማሻሻያ እና የአቅም ማሳደግ ሥራ ለአብነት አንስተዋል።

አቶ ምትኩ እንዳሉት በሶዶ ከተማና አካባቢው ያለውን የኃይል ተጠቃሚ ቁጥር በማደጉ በከተማዋ በሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ተጨማሪ ሁለት ትራንስፎርመሮችን ለመትከል ታቅዷል።

ይህም በቀጣይ የሚመጣውን ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት ጥያቄ በአግባቡ ለማስተናገድ ያስችላል ብለዋል፡፡

በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች በተጨማሪ በሪጅኑ በቀጣይ ሊመጡ የሚችሉ የኃይል ፍላጎት ጥያቄዎችን ታሳቢ በማድረግ ተቋሙ አዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ግንባታ እና የማስፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አቶ ምትኩ አስረድተዋል፡፡

ሥራዎቹ ሲጠናቀቁ በሪጂኑ ስር ለሚገኙ  አካባቢዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እና ተደራሽነትን  ለማስፋፋት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የወላይታ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ መና በበኩላቸው ከከተሞች እና ከኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚመጡ የኃይል ጥያቄዎችን ለመመለስ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም አስቀድሞ ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በሶዶ ከተማ ያሉ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለሚቀርቡ የኃይል ጥያቄዎች በቀላሉ ምላሽ እንዲሰጥ ከማስቻላቸውም ባለፈ  የኃይል መቆራረጥ እና የቮልቴጅ መዋዠቅ ሳይኖር የሚፈለገውን ኃይል ለማቅረብና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እያገዙ መሆኑን አብራርተዋል።

የደቡብ ሁለት ሪጅን የኃይል አቅርቦት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ሙሉ በሙሉ እንዲሁም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን በከፊል የሚሸፍን ሲሆን ሪጅኑ የሶዶ ኮንቨርተር ጣቢያን ጨምሮ የተለያየ የኪሎ ቮልት መጠን  ያላቸው ስምንት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና 1 ሺህ 180  ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመሮችን ያስተዳድራል።

Scroll to Top