ተጠርጣሪዎችን የተለያዩ ፖሊሳዊ የምርመራና ክትትል ስልቶችን በመጠቀም በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

ተጠርጣሪዎችን የተለያዩ ፖሊሳዊ የምርመራና ክትትል ስልቶችን በመጠቀም በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

ከይርጋለም ቁጥር 2- ሐዋሳ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ በተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥምር የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ ስርቆት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።

በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የቱላ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር ማቴዎስ ወንድሙ እንደገለፁት በሀገር ሀብት ላይ ስርቆት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎችን የተለያዩ ፖሊሳዊ የምርመራና ክትትል ስልቶችን ተጠቅሞ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሥራዎች ተጀምረዋል።

ከህብረተሰቡ በሚገኘው መረጃ መሠረት ክትትል በማድረግ የተሰረቁ ንብረቶችን በህግ አግባብ ለማስመለስ እንደሚሰራ አዛዡ አረጋግጠዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚሰራው ሥራ ላይ ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋም ደህንነት መምሪያ የደቡብ አንድ የፊዚካል ሴኪዩሪት አስተዳደር ባለሙያ ኮሎኔል ኤርሚያስ ደሳለኝ በበኩላቸው በሪጅኑ ስርቆት የሚፈፀምባቸውን አካባቢዎች በመለየት በየደረጃው ከሚገኙ የመስተዳደር እና የፀጥታ አካላት እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለኃይል መሠረተ ልማቶች ጥበቃ እንዲደረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

ምንም እንኳ የመሠረተ ልማቶቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ ውይይቶች ቢካሄዱም በሲዳማ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ላይ አሁንም ስርቆት እየተፈፀመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የብረት ምሰሶው መውደቅ መረጃ እንደደረሳቸው አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በሲዳማ ዞንና በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በየደረጃው ለሚገኙ የመስተዳድር እና የፀጥታ አካላት ማሳወቃቸውን ተናግረዋል። 

Scroll to Top