በአርባ ምንጭ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኘው የባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የከተማዋን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እና ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነቃቃው የከተማ አስተዳደሩ ገለፀ።
የከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደብል ደሳለኝ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ በሆቴል፣ በኢንዱስትሪ እና በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ትልቅ ተስፋ የፈጠረ በመሆኑ ለዘርፉ ዕድገትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።



ከተማዋ በአሁኑ ወቅት በተለይም በሆቴልና በኢንዱስትሪ ዘርፎች በርካታ ባለሀብቶችን እየሳበች ትገኛለች ያሉት ኃላፊው ለዚህም የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቱ ግንባታ ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
የጣቢያው መገንባት የከተማዋን አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ፍላጎት እና አቅም አሁን ካለበት አንድ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገውም አቶ ደብል አስታውቀዋል።
በከተማዋ በሆቴል ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ማሞ ደቦጭ በበኩላቸው በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ ለደንበኞች የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በከተማው እየተገነባ ያለው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለነገው አገልግሎታቸውና ለሥራቸው መስፋፋት ትልቅ ተስፋ እንዲሰንቁ ማድረጉን ተናግረዋል።
ሌላዋ በሆቴልና በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ሽታዬ ዘካርያስ ደግሞ አብዛኛው የሆቴልም ሆነ የግብርና ሥራቸው በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ማከፋፈያ ጣቢያው ዘመናዊ አሰራርን በመከተል ለደንበኞቻቸው የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚያግዛቸው አብራርተዋል።
ዘመናዊ ግብርናን ለማስፋፋት የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ሺታዬ የግብርና ሥራቸውን ወደ ላቀ የዘመናዊነት ደረጃ ለማሸጋገር በጣቢያው ላይ ትልቅ ተስፋ መጣላቸውንም አስረድተዋል።
ወይዘሮ ሽታዬ እንዳሉት በአሁን ወቅት በሆቴል ዘርፍ ብቻ ከ30 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ በቀን ከ50 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል።
እየተገነባ ያለው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ስራቸውን ይበልጥ በማስፋፋት ለበርካታ ዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አረጋግጠዋል።

