በደቡብ 1 ሪጅን በየጊዜው እያደገ ለሚሄደው የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በይርጋለም ቁጥር 2፣ በሐዋሳ ቁጥር 2 እና በዲላ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የትራንስፎርመሮችን አቅም ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን በሪጅን የማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ያለው አማረ እንደተናገሩት የሐዋሳ ቁጥር 1 እና የዲላ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከተሞቹ አሁን ለደረሱበት ዕድገት ሚናቸው የጎላ ነው።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት የሐዋሳ ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያን ጨምሮ በሪጅኑ የሚገኙ አብዛኛዎቹ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ጭነታቸው ከ90 በመቶ በላይ በመድረሱ የሚቀርቡ ተጨማሪ የኃይል ፍላጎቶችን በአግባቡ ማስተናገድ የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በየጊዜው እያደገ ለሚሄደው የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በይርጋለም ቁጥር 2፣ በሐዋሳ ቁጥር 2 እና በዲላ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ተጨማሪ ትራንስፎርመሮችን በመትከል አቅማቸውን ለማሳደግ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
የማከፋፈያ ጣቢያዎችን የኦፕሬሽን ሥራ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማከናወን ረጅም ዓመት ያገለገሉ ጣቢያዎችን የመቆጣጠሪያ ብሬከሮች እና ሲዊች ያርድ ላይ የሚገኙ የተለያዩ የመቆጣጠሪያ ዕቃዎችን በተሻሻሉና ዘመኑን በዋጁ መሳሪያዎች ለመቀየር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ያለው ገለፃ የማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅማ ማሳደግና ማዘመን ሥራዎች እስኪከናወኑ ድረስ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመነጋገር የኃይል አቅርቦቱን ሊያስቀጥሉ የሚችሉ አሰራሮችን በመተግበር እየተሰራ ይገኛል ።

