ግድቡ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቶች ላይ ትልቅ እሴት የሚጨምር ነው -የቱሪዝም ሚኒስቴር

ግድቡ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቶች ላይ ትልቅ እሴት የሚጨምር ነው -የቱሪዝም ሚኒስቴር

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ እስካሁን ከነበሯት የቱሪዝም ሀብቶች ላይ ትልቅ እሴት የሚጨምር መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ አስታወቁ።

ሚኒስትር ዲኤታው እንደገና አበበ (ዶ/ር ) እንዳስታወቁት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የሠንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት እና ኢትዮጵያውያን ፅናታቸውን ያሳዩበት እንደ አፍሪካ ደግሞ ከአድዋ በኋላ ለፓን አፍሪካ ንቅናቄ ያዋጣነው ትልቅ ሀብት ነው።

የህዳሴ ግድብ በቱሪዝም እሳቤ ውስጥ የሚመጡ ሁለት ነገሮችን ያሟላ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዲኤታው  የመጀመሪያው  ተጨባጭ የሆነና በአካል የሚታይ ሲሆን  ሁለተኛው የሚነገርለት ታሪክ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትር ዲኤታው ገለጻ  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የፈጠረው ንጋት ሀይቅን ጨምሮ የሌሎች ደሴቶች አካላዊ ዕይታ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ፍሰት ትልቅ ተስፋ ይዞ መጥቷል።

በተጨማሪም ግድቡን  በራሳችን ሀብት እና ልጆች  በብዙ ጫና ውስጥ ሆነን ማጠናቀቃችን ኢትዮጵያዊያን መሥራት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት በመሆኑ ትርክቱ በራሱ ትልቅ የቱሪዝም መስህብ መሆኑን አስረድተዋል።

ግድቡ ከቱሪዝም ባሻገር ኢንቨስትመንትን በመሳብ  ለኢትዮጵያ ብዙ ሀብት ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይህን ታሳቢ ያደረገ የሮድ ማፕ ጥናት እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቱሪዝሙን ለማሳደግ በህዳሴ ግድቡ ላይ ለሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ሚኒስትር መስሪያ ቤታቸው ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም ነው ያመለከቱት።

አስጎብኚ ድርጅቶች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሂደው በማየትና በፓኬጃቸው ውስጥ በማካተት ለዓለም ህዝብ እንዲያስተዋውቁ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ሚኒስትር ዲኤታው አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ያሏት ሰፊ ሃገር በመሆኗ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ግድቡን በመጎብኘት ሀሳብ እንዲወስዱና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top