ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአዲሱ ትውልድ ፓን አፍካኒዝም ነው – የቀድሞ የአፍሪካ የነጻነት ታጋዮች ልጆች

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአዲሱ ትውልድ ፓን አፍካኒዝም ነው – የቀድሞ የአፍሪካ የነጻነት ታጋዮች ልጆች

ኢትዮጵያ ገንብታ ያጠናቀቀችው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ቀደምት አፍሪካውያን አባቶቻችን ሲመኙት የነበረውን ርዕይ እውን ያደረገ፣ አፍሪካን ዳግም ወደ አንድነት የሚያመጣ የአዲሱ ትውልድ ፓን አፍሪካኒዝም መሆኑን የቀድሞ የአፍሪካ የነጻነት ታጋዮች ልጆች  ገለጹ።

በአፍሪካ ታዋቂ የሆኑ የነጻነት ታጋዮችና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪዎች ልጆች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ጎብኝዎቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካውያን ትልቅ የመቻል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀድሞው የጋና የነጻነት ታጋይ የክዋሚ ንክሩማ ልጅ ሳሚያ ንኩርማ አፍሪካውያን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ጉዳዮች አንድ ሆነው ማየት የአባታቸው የዘወትር ህልም እንደነበር አስታውሰዋል።

ስለሆነም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አፍሪካውያን በሁሉም ዘርፎች ቢጀምሩም ማጠናቀቅ አይችሉም የሚለውን የተሳሳተ ትርክት መለወጥ የሚችል ከኢትዮጵያም አልፎ ለመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት መሆኑን አብራርተዋል።

የቀድሞ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ ልጅ ማዳርካ ኔሬሬ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በታንዛኒያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈረመውን የኃይል ሽያጭ ስምምነት እውን በማድረግ በቀጣናው የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር የፓን አፍሪካኒዝምን እሳቤ በአዲሱ ትውልድ ውስጥ ለማስረጽ እና  የፓን አፍሪካን አባቶችን ሌጋሲ ለማስቀጠል ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ከደቡብ አፍሪካ የመጡት እና የቀድሞው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኦሊቨር ታምቦ ልጅ ኖማቴምባ ታምቦ ኢትዮጵያ ህዝቦቿን አስተባብራ በራሷ የፋይናንስ አቅም ይህን ታላቅ ግድብ ገንብታ ማጠናቀቋ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህ ጥንካሬና ፅናት ለሌሎች አፍሪካውያንም ትልቅ መነሳሳት ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ብዙ  ውስብስብ ችግሮችን በመፍታት ፅናታቸውን ለዓለም ህዝብ ያስመሰከሩበት እንደሆነ ማረጋገጣቸውን ጎብኝዎቹ መስክረዋል።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ የነበራትን አስተዋጽኦ እንደሚያውቁ አስታውሰው በቀጣይም  አፍሪካን አንድ የማድረግ የአባቶቻቸውን ሌጋሲ እውን ለማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በጉብኝቱ ታዋቂው የጋና የነጻነት ታጋይ ኩዋሚ ንኩሩማ ልጅ ሳሚያ ንኩሩማ እና የቀድሞ የታንዛኒያ የነጻነት ቀንዲልና  ፕሬዚዳንት የነበሩት የጁሊየስ ኔሬሬ ልጅ ማዳርካ ኔሬሬ ልጅን ጨምሮ የቀድሞ የሊቢያ መሪ መሃመድ ጋዳፊ፣ የቀድሞ የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ኬኔት ካውንዳ፣ የፓትሪስ ሉምባ እና ሌሎች የአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪዎች ልጆች ተሳትፈዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top