ግድቡ በራስ አቅም የመልማት አቅማችን ዐቢይ ማሳያ ነው‎

ግድቡ በራስ አቅም የመልማት አቅማችን ዐቢይ ማሳያ ነው‎

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ በራስ አቅም የመልማት አቅማችን ዐቢይ ማሳያ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

‎ተቋሙ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅንና ለምርቃት መዘጋጀትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በስካይ ላይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

‎መግለጫውን የሰጡት የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ዳግማዊ ዓድዋ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምርቃት ዝግጁ ሆኗል።

‎ግድቡ ከፋይናንስ ምንጩ፣ በሚይዘው የውሃ መጠን፣ በሚሰጠው ትርጉም ከሌሎች የኃይል ማመንጫዎች ልዩ እንደሚያደርገው ገልፀዋል።

እስካሁን ያለው ‎የግድቡ ግንባታ ወጪ ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑንና ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መሸፈኑን የጠቆሙት አቶ ሞገስ ከዚህ ውስጥ 91 በመቶው ከንግድ ባንክ እንዲሁም ቀሪው 23 ቢሊዮን ብሩ ወይም 9 በመቶው በሕብረተሰብ ተሳትፎ የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ከፋይናንስ ተሳትፎ በተጨማሪ ሕብረተሰቡ በዕውቀት፣ በዲፕሎማሲ፣ በጉልበት እና በሀሳብ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው አብራርተዋል።

ይህም ግድቡ በጫናዎች ሳንበገር በፍትሐዊነት በራሳችን አቅም የመልማትና ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅ ጽኑ ፍላጎታችንን ለዓለም ያሳየ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለምርቃ ዝግጁ መሆኑን ያወሱት አቶ ሞገስ በህዳሴ ደዴሳ ሆለታ እና በበለስ መስመር በኩል ኃይሉ ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት እየገባ መሆኑን አብራርተዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top