ጉዳት ደርሶበት የነበረው የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር ተጠግኗል

ጉዳት ደርሶበት የነበረው የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር ተጠግኗል

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቱሉቦሎ አካባቢ ጉዳት ደርሶበት የነበረው የማስተላለፊያ መስመር እና ለግንኙነት የሚያግዘው ኦፕቲካል ፋይበር (OPGW) ተጠግኖ ወደ ሥራ መግባቱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይበር ኦፕቲክስ የኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ገለፀ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ኤርሚያስ ገብረ መድህን እንደገለፁት የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮቹ ለኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መከላከያ ከመስጠት ባለፈ ለቴሌኮሙዩኒኬሽን ሥራዎች እንዲሁም ከኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች መረጃዎችን ወደ ብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ለማድረስ ይረዳሉ።

ከጊቤ ሁለት – ሰበታ ሁለት ባለው ባለ 400 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ላይ ተዘርግተው በሚገኙ የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች በጉዳት ምክንያት አገልግሎቱ ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ጉዳት በደረሰበት መስመር ኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ የፋይበር ኦፕቲክስ ተከራይተው ይጠቀሙ እንደነበር አቶ ኤርሚያስ አስታውሰዋል።

በደረሰው ጉዳት የተነሳ አገልግሎቱ ተቋርጦ ጥገና ሳይደረግለት መቆየቱን እና የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከሉ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያሉ መረጃዎችን መሰብሰብና መመልከት አለመቻሉን አብራርተዋል፡፡

የተቋሙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ መስመሩን ጠግኖ ወደ ሥራ ማስገባቱን ተናግረዋል፡፡

የጥገና ሥራው በጥቂት ቀናት እንዲጠናቀቅ እገዛ ያደረገውን ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አመስግነዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top