ስድስት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች በመውደቃቸው ኃይል ተቋርጧል

ስድስት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች በመውደቃቸው ኃይል ተቋርጧል

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ልዩ ስሙ መቃ በተባለ አካባቢ በስርቆት እና ከባድ ንፋስ ቀላቅሎ በጣለ ዝናብ ምክንያት በከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ ጉዳት መድረሱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን አስታወቀ።

በሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይነህ ልጅዓለም እንዳስታወቁት በተፈፀመው ስርቆት እና ንፋስ ቀላቅሎ በጣለው ዝናብ ምክንያት ከአዘዞ-ሸኽዲ በተዘረጉ ስድስት ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በዚህም ምክንያት ከሸኽዲ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ ሲያገኙ የነበሩ ከተሞችና አካባቢዎች በሙሉ የኃይል አቅርቦት በጊዜያዊነት እንደተቋረጠባቸው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የወደቁትን የብረት ምሰሶዎች ለመጠገን የጥገና ባለሙያዎች ወደ ስፍራው ማቅናታቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡

የኃይል መቋረጡን በጊዜያዊነት በእንጨት ምሰሶዎች ለመተካት  ጥረት መጀመሩን የጠቀሱት አቶ አባይነህ ከተዘጋጁት 84 የእንጨት ምሰሶዎች መካከል በአሁኑ ወቅት የስድስት የእንጨት ምሰሶዎች ተከላ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የወደቁትን የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች በአፋጣኝ በመጠገን በአጭር ጊዜ የኃይል አቅርቦቱን ለማስቀጠል ጥረት ተጀምሯል፡፡

በመሆኑም ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ የአካባቢው ነዋሪዎች በትዕግስት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሪጅኑ ከአንድ ዓመት በላይ የኃይል አቅርቦቱ ተቋርጦ የቆየውን የማርቆስ-ሞጣ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዳግም ወደ ኦፕሬሽን ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top