የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኃይል ማመንጫዎች፣ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና ማስተላለፊያ መስመሮች ኦፕሬሽን ዘርፍ ለተውጣጡ ሠራተኞች የአሰልጣኞች ሥልጠና መስጠት ጀመረ።
በኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በሦስት ዙር ተከፋፍሎ ለአስር ቀናት የሚሰጠውን ሥልጠና የመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞች ትናንት ሥልጠናቸውን ጀምረዋል።
በተቋሙ የሰው ኃይል ስልጠና እና ልማት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምስ ሰይፉ በስልጠናው ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ እንደገለጹት ሥልጠናው በዋናነት ሰልጣኞች ከሥልጠና በኋላ የስልጠና አሰጣጥ ጥበብ እና ስልቶችን ተከትለው እውቀታቸውን በተገቢው መንገድ ለሌሎች ማስተላለፍ እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
በተቋሙ የብዙ ልምድ ባለቤት የሆኑ አንጋፋ ሠራተኞች የሚገኙ ቢሆንም ያላቸውን እውቀትና ልምድ ለሌሎች በማካፈል ረገድ ውስንነቶች እንደነበሩ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ሥራ አስኪያጁ በነባር የተቋሙ የሰው ኃይል እና አዲስ በሚቀላቀሉ ሠራተኞች መካከል ከ15 እስከ 20 ዓመት የሚደርስ የዕድሜ ክፍተት እንዳለ በጥናት መረጋገጡን ጠቅሰው ይህም ሰፊ የእውቀት ክፍተት እና ልዩነት እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ስለሆነም በተቋሙ የውስጥ አቅም ስልጠናን በማሳደግ እና በሁሉም ዘርፎች ተደራሽ በማድረግ የእውቀት ክፍተት እንዳይፈጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የተቋማዊ ትራንስፎርሜሽን ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱዓለም ኪዳኔ በበኩላቸው በአስተዳደራዊ እና በቴክኒክ ዘርፉ ላይ ያሉ እውቀቶችን በመጠቀም የተቋሙን ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ማሳካት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ተቋሙ በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ካስቀመጣቸው ግቦች ለመድረስ የሰው ኃይል አቅም ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ ሁሉም የተቋሙ አመራርና ሠራተኛ የሚሰጡ ስልጠናዎችን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ስልጠናን በተቋሙ የውስጥ አቅም በመስጠት ብቃት ያለው የሰው ሀብት ለመገንባት በኦፕሬሽን ዘርፉ ላይ የተጀመረው የአሰልጣኞች ስልጠና በቀጣይ በተቋሙ ሁሉም ዘርፎች የሚሰጥ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በማከፋፈያ ጣቢያዎች የትራንስፎመሮችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚስችል ስልጠና ለማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና ባለሙያዎች እየሰጠ ይገኛል፡፡
በተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝንስ ዘርፍ የትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድርያስ እንደገለፁት ሥልጠናው በየማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚገኙ ትራንስፎርመሮች ከብልሽት የፀዱና ደኅንነታቸው የተጠበቁ እንዲሆኑ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
በመላው ሀገሪቱ ከሚገኙ 154 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ ከ45 በላይ የሚሆኑት ከአቅም በላይ የኃይል ጭነት የተሸከሙ በመሆናቸው ጥብቅ የደኅንነት ክትትልና የፍተሻ ሥራ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
በተቋሙ የፓወር ግሪድ ትንተና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑትና ሥልጠናውን እየሰጡ ያሉት አቶ አበባው ጋሻው በበኩላቸው ሥልጠናው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ትራንስፎርመሮችን የአገልግሎት ዘመናቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





