ሪጅኑ የእንጨት ምሰሶዎችን በብረት ምሰሶ እየቀየረ ነው

ሪጅኑ የእንጨት ምሰሶዎችን በብረት ምሰሶ እየቀየረ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ ሁለት ሪጅን በስርቆት ምክንያት ወድቀው በጊዜያዊነት በእንጨት ምሰሶ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን በብረት ምሰሶዎች እየቀየረ መሆኑን ገለጸ።

በሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመሮች እና ኦፕቲካል ፋይበር ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎሳዬ ደምሴ  እንደገለጹት በሪጅኑ በአዋሽ – አሰላ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ በተፈጸመ ስርቆት ምሰሶው ወድቆ ነበር።

ሪጅኑ አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ለማድረግ የወደቁ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን በእንጨት በመተካት በጊዜያዊነት አገልግሎቱን ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ የአዋሽ – አሰላን የእንጨት የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን በብረት በመቀየር ወንጂ ስኳር ፋብሪካ፣ አሰላ እና አካባቢው የሚገኙ ዞንና ወረዳዎች ከትናንት እኩለ ቀን ጀምሮ ያልተቆራረጠና አስተማማኝ ኃይል እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል።

ሪጅኑ በመቶ ቀን ዕቅዱ የአዋሽ – አሰላ የማስተላለፊያ መስመርን ጨምሮ ሌሎች በጊዜያዊ የእንጨት ምሰሶዎች አገልግሎት እየሰጡ ያሉትን የቆቃ – ቢሾፍቱ- ገላን እና ቃሊቲ ባለ 132 ኪሎ ቮልት እንዲሁም አዳማ ሁለት – አዋሽ 7 ኪሎ ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመሮች በብረት ምሰሶ ለመቀየር እየሰራ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ሪጅኑ  የተቋረጡትን የመተሀራ – መልካ ጅሎ የባቡር መስመር እና ቃሊቲ – ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ባለ 132 ኪሎ ቮልት መስመሮች  ወደ ኦፕሬሽን እንዲገቡ ለማድረግ  እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top