ያለ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚከናወን የልማት እንቅስቃሴም ሆነ ሃገራዊ ዕድገት እንደሌለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋማዊ ደህንነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ከሊል ሽፋ ገለፁ
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምሥራቅ አንድ ሪጅን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ደህንነትን ለማስጠበቅ ከአካባቢው የመስተዳድር፣ የፍትህና ፀጥታ አካላት እና ከማህበረሰቡ ተወካዮች ጋር በድሬዳዋ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሂዷል።



ውይይቱ በከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን እና መሰረተ ልማቶቹ በተገነቡበት ቦታዎች የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ግንባታዎችን እንዴት ማስቆም እንደሚቻል ግንዛቤ ለመፍጠርና የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው።
በውይይቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት አቶ ከሊል ሽፋ በተቋሙ ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን ለመከላከል በሁሉም ሪጅኖች የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ተመድበው እየሰሩ ይገኛል።
ስርቆትን በመከላከል የተቋሙን ንብረት ደህንነት ለማስጠበቅ ከአካባቢው መስተዳድሮች፣ ከክልሎችና ከፌደራል የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ስለ መሆኑም አቶ ከሊል አስረድተዋል።
ተደጋጋሚ ስርቆት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ተቋሙ በራሱ ወጭ እስከማስጠበቅ መድረሱን ያወሱት ዳይሬክተሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም የጋራ ኃላፊነት መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ምስራቅ ቀጠና አዛዥ ኮማንደር ምትኩ ዳባ በበኩላቸው እያንዳንዱ ዜጋ የመሠረተ ልማቱ ባለቤት መሆን እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው በመሠረተ ልማት ላይ ስርቆት የሚፈጽሙ አካላት ከማህበረሰቡ ዕይታ ውጭ ባለመሆናቸው ሁላችንም ልናጋልጥና ለህግ አካላት ልንጠቁም ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

በዚህ ዕኩይ ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላት ከሀገር ጠላት ጋር እኩል መሆኑን አስረድተው ይህን መጥፎ ድርጊት በጋራ መታገልና ማስቆም ያስፈልጋል፡፡ ያሉት ኮማንደሩ ስርቆት በሚፈፁሙ አካላት ላይ በሚወሰዱ ህጎች ላይም መሻሻል ይገባል ሲሉ ኮማንደሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽሕፈት ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ዶ/ር ሰይፉ ታደሰ በበኩላቸው የመሰረተ ልማት ስርቆትን ከመነሻው እስከ መድረሻው ጀምሮ ያለውን ሰንሰለት በመለየትና ህጋዊ የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ዶ/ር ሰይፉ አክለውም እንደ ከተማ አስተዳደር በከተማዋና በዙሪያዋ የሚፈፀሙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆቶችን በምንም መልኩ እንደማይታገሱና ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው ገልፀዋል።
በሪጅኑ የመሠረተ ልማት ስርቆትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የአካባቢው የመስተዳድር እና የፀጥታ አካላት ለጉዳዩ ለሚሰጡት ትኩረት ምስጋና ያቀረቡት የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ወርዲ መሃመድ ይህ ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ሪጅኑ የሚያስተዳድራቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ሰፊ ሽፋን ያላቸውና ብዙ ርቀትን የሚያቋርጡ በመሆናቸው በተቋሙ ብቻ የሚደረግ ጥበቃ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ጠቅሰው ሁሉም አካል መሠረተ ልማቶችን በባለቤትነት ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በአካባቢው የሚፈጸሙ ስርቆቶች ከግንዛቤ እጥረት የሚመነጩ መሆናቸውን ጠቅሰው በጉዳዩ ላይ የግንዛቤ ሥራ በስፋት መሠራት እንዳለበት ገልፀዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የድሬዳዋ ከተማና በዙሪያው ያሉ የአካባቢው መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎች፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት እና
የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


