በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ሥር ከሚገኙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለኅብረተሰቡና ለኢንዱስትሪዎች አገልግሎት የሚውል በቂ ኃይል እየቀረበ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጅማ ሪጅን አስታወቀ::
በአገልግሎቱ የጅማ ሪጅን የማሰራጫ መስመሮች ኦፕሬሽንና ጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ሻምበል አድማሱ እንደገለፁት ሪጅኑ ከወልቂጤ ማከፋፈያ ጣቢያ በአንድ ወጪ መስመር የሚያገኘውን ጨምሮ በአጠቃላይ ከስድስት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል እየተቀበለ ይገኛል።
የጅማ ሪጅን ከእነዚህ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚነሱ 22 የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችን በመጠቀም በሪጅኑ ለሚገኙ ደንበኞች በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በማቅረብ ላይ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።



በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማከፋፈያ ጣቢያዎችን የቁጥጥር ሥርዓት የማዘመን ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል።
ይህ የማዘመን ሥራ በመስመሮቹ ላይ የሚከሰቱ ብልሽቶችንና መቆራረጦችን በፍጥነት በመለየትና ለመፍታት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ሻምበል አስረድተዋል።
ይህ የቴክኖሎጂ ማሻሻያ በተለይም እንደ ሊሙ ለመሳሰሉ ከማከፋፈያ ጣቢያ በረጅም ርቀት ለሚጓዙ የኃይል ማሰራጫ መስመሮች ላይ ብልሽቶች ሲፈጠሩ ችግሩን በቀላሉ ተቆጣጥሮ ለመጠገን ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ እያከናወናቸው ያሉ የአቅም ማሳደግና የማዘመን ሥራዎች በአገልግሎቱ ደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎችን እየቀረፉ እንደሚገኝ የጠቀሱት ኃላፊው ተቋሙ በቀጣይም ይህን በጎ ጅምር አጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸውን አቶ ሻምበል ገልፀዋል።
ለኅብረተሰቡ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ሲባል ሁለቱ ተቋማት በኃይል አቅርቦት ላይ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው የሰው ኃይላቸውንና ማሽነሪዎቻቸውን በማስተባበር በጋራና በትጋት እየሠሩ እንደሚገኙ ኃላፊው ተናግረዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


