በማከፋፈያ ጣቢያው የኃይል ፍላጎት በማደጉ የአቅም ማሳደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ

በማከፋፈያ ጣቢያው የኃይል ፍላጎት በማደጉ የአቅም ማሳደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ

በአካባቢው ካለው የከተሞችና የኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በሚዛን ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ያለው የኃይል ጭነት በፍጥነት እያደገ መምጣቱን የጣቢያው ኃላፊ ወ/ሮ ፀጋነሽ ሞላ ተናግረዋል

ማከፋፈያ ጣቢያው በአሁኑ ወቅት 6 ነጥብ 3 እና 25 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል መሸከም የሚችሉ ሁለት ትራንስፎርመሮች ያሉት ሲሆን በ132 ኪሎ ቮልት የተቀበለውን ኃይል በስድስት ባለ 15 እና ባለ 33 እንዲሁም በአንድ ባለ 66 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች አማካኝነት እያቀረበ ይገኛል።

የጣቢያው ኃላፊ እንዳብራሩት በሦስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ለሚዛን፣ ሸኮ፣ አማን ከተሞችና አካባቢዎቻቸው ኃይል የሚሰራጭ ሲሆን በ33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ደግሞ ለዲማ፣ ጨና 1 እና 2፣ ባቹማ፣ ሸዋ ቤንች ከተሞችና አካባቢዎች እስከ ጋምቤላ ክልል ድረስ ኃይል ያቀርባል።

በአካባቢው የከተሞች መስፋፋት፣ የወርቅ ማዕድናት ፍለጋ እና የቡና መፈልፈያ ኢንዱስትሪዎች በመበራከታቸው የጣቢያው የኃይል ጭነት በየጊዜው እያደገ መጥቷል ብለዋል።

የ15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ከሁለት ዓመት በፊት ከነበራቸው የ2 ነጥብ 83 ሜጋ ዋት ጭነት በአሁኑ ወቅት ወደ 6 ነጥብ 19 ሜጋ ዋት ከፍ ማለቱን የገለፁት ኃላፊዋ በተመሳሳይ የ33 ኪሎ ቮልት መስመሮች ጭነት ከ2 ሜጋ ዋት ወደ 4 ነጥብ 75 ሜጋ ዋት አድጓል።

በአሁኑ ወቅት ለባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ኃይል እየሰጠ ያለው የ 6 ነጥብ 3 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሩ ጭነት በመሙላቱ ምክንያት በጣቢያው ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

እስከ አሁን ባለው ሂደት በመቆጣጠሪያ ክፍሉ ውስጥ የሚገጠሙ የፕሮቴክሽን መሣሪያዎች፣ ከቤት ውጭ የሚሰሩ የትራንስፎርመር ማስቀመጫዎችና ሌሎች የማስፋፊያ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል።

አዲሱ ትራንስፎርመር ጣቢያው ላይ ሲደርስም የመግጠም እና የማገናኘት ሥራው ወዲያውኑ እንደሚከናወን ኃላፊዋ ገልፀዋል።

ይህ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት የአቅም ማሳደግ ሥራ ተከናውኖለት እንደማያውቅ ተገልጿል።

Scroll to Top