የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመላው አገሪቱ የሚያከናውናቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ማህበረሰቡን ባቀፈ መልኩ የሚሰሩ መሆናቸውን አስታወቀ
ተቋሙ ይህንን የገለፀው የምስራቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪሲቲ ማጠናከሪያ ፕሮጀክትን በቅርቡ ለማስጀመር የሚያስችል የጋራ ውይይት ከአካባቢው የመስተዳድር አካላት ጋር ባካሄደበት ወቅት ነው።



ውይይቱ በዋናነት ከይዞታ አሰጣጥ ጋር ተያይዘው የነበሩ የቆዩ ተግዳሮቶችን በመፍታት ግንባታውን በፍጥነት ለማስጀመር በሚያስችሉ የጋራ መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ ነው።
ተቋሙ ከሐረር ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ለሚገነባው ማከፋፈያ ጣቢያ የሚሆን ቦታ ከአሁን በፊት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ወደ ኋላ የተመለሰበትን ምክንያት የአካባቢው የመስተዳድር አካላት ማብራሪያ እንዲሰጡበት በውይይቱ ላይ ጠይቋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ ሚስኪ መሐመድ ለፕሮጀክቱ የተጠየቀው ቦታ እስካሁን ያልተፈቀደበትን ዋና ምክንያት ሲያስረዱ በልማቱ ለሚነሱ የአካባቢው አርሶ አደሮች ማኅበራዊ መረጋጋት ለመፍጠር ሲባል በመተላለፉ ነው።
ይህም ፕሮጀክቱ ሊያርፍበት በታሰበው መሬት ላይ ያሉ አርሶ አደሮች ከአሁን በፊት ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ሲባል በተደጋጋሚ የተነሱ በመሆናቸው አሁንም በድጋሚ አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ ቢደረግ ነዋሪዎቹን ለማህበራዊ አለመረጋጋት ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ሂደቱ ሊዘገይ ችሏል።



ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከማንኛውም የይገባኛል ጥያቄ ነፃ የሆነ የተሻለ የመንግሥት መሬት በአማራጭነት መዘጋጀቱን ወ/ሮ ሚስኪ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከባቢሌ ወረዳ አመራሮች ጋር በመነጋገር ይህንን ምትክ መሬት እንዲረከብም የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል።
የባቢሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑሬ መሐመድ በበኩላቸው በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የልማት ጥማት ለመመለስ የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ መሆኑን ገልፀው የተመረጠውን አዲስ አማራጭ መሬት ለመተግበር ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋማዊ ደህንነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ከሊል ሽፋ ተቋሙ የሚያከናውናቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግንባታዎች የሕዝብን የልማት ጥያቄ የሚመልሱ መሆናቸውን አስገንዝበው የቀረበውን አማራጭ በፍጥነት በማየት ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጀመርበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል።
የምስራቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪሲቲ ግሪድ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ሙሉብርሃን በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የምስራቁን ክፍል በግሪድ ከማስተሳሰሩ ባሻገር በአካባቢው ለሚገነቡ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችና ለማህበረሰቡ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
በመሆኑም የባቢሌ ወረዳ በአማራጭነት የተሰጠውን ቦታ በአስቸኳይ ነፃ አድርጎ እንዲያስረክብና ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጀመር ጠይቀዋል።
ይህን ታላቅ አገራዊ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ለሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች ተቋሙ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸፀል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የዚህ ፕሮጀክት አካል የሆኑት የፋፈን እና ጅግጅጋ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚገነቡበት ቦታና ሌሎች የቅድመ ግንባታ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል።


