በሃይንከን ኢትዮጵያ ስር ለሚገኘው ለበደሌ ቢራ ፋብሪካ እየቀረበ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል የፋብሪካው ማሽኖች ደህንነታቸው ተጠብቆ ምርታማ እንዲሆኑ እያስቻለ መሆኑን የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ ተገኑ ዲባባ ገለፁ።
ሥራ አስኪያጁ እንደገለፁት ፋብሪካው ቀጥታ ከበደሌ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ለብቻው በተዘረጋ በባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመር ኃይል እያገኘ ነው። ይህም ለምርት እንቅስቃሴው የሚያስፈልገውን በቂ ኃይል ሳይቆራረጥ በአግባቡ እንዲያገኝ አስችሎታል።
አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት መኖሩ ማሽነሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለረጅም ጊዜ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ በማስቻል የፋብሪካው ምርታማነት ከጊዜ ወደጊዜ እንዲጨምር አድርጎታልም ብለዋል ።



በተጨማሪም በኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚከሰቱ የምርት ብክነቶችን እና የማሽን ብልሽትን በማስቀረት ማሽኖቹ ያለማቋረጥ የሚጠበቅባቸውን ምርት እንዲያመርቱ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ስለመሆኑም አቶ ተገኑ ጠቅሰዋል።
ሁሉም የፋብሪካው ማሽኖች ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል መንቀሳቀስ እንደማይችሉ፤ ቢንቀሳቀሱ እንኳን ዘላቂነት እንደማይኖራቸው የገለፁት ሥራ አስኪያጁ የኃይል አቅርቦቱ የነዳጅ አጠቃቀምን በመቀነስና ምርታማነቱን በማሳደግ ፋብሪካውን ውጤታማ እያደረገው እንደሚገኝም አስረድተዋል ።
የኃይል አቅርቦት ለፋብሪካው “የደም ስር” ነው ያሉት አቶ ተገኑ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ አስተማማኝ ባይሆን ኖሮ አሁን ባለው ሁኔታ ፋብሪካው ለከፍተኛ የነዳጅ ወጭ መዳረግ ብቻ ሳይሆን ለምርት ማቋረጥ የሚጋለጥበት አጋጣሚ የሰፋ እንደነበርም አንስተዋል ።
በፋብሪካው የዩቲሊቲ ሥራ አስኪያጅ አቶ አቤል ዋኘው በበኩላቸው ፋብሪካው የሥራ እንቅስቃሴውን ለማስኬድ በዓመት በአማካኝ 5 ሺህ ሜጋ ዋት ሰዓት ኃይል እንደሚጠቀም ገልፀዋል።
እየቀረበ ያለው የኃይል መጠን አሁን ባለው የምርት ሂደት የፋብሪካውን ማሽኖች በአግባቡ እያንቀሳቀሰ እንደሆነም ጠቁመዋል። የኃይል አቅርቦቱ ፋብሪካው ወደ ከባቢ አየር የሚለቀውን የበካይ ጋዝ በመቀነስ ለአከባቢ ጥበቃ አስተዋፅኦ እያደረገ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
የበደሌ ቢራ ፋብሪካ አሁን ላይ በዓመት ከ600 ሺህ ሄክቶ ሊትር በላይ እያመረተ እንደሆነ ተገልጿል።





