ተቋሙ እያከናወናቸው ያሉ የኃይል ተደራሽነት ሥራዎች የማህበረሰቡን ቅሬታ እየፈቱ ነው

ተቋሙ እያከናወናቸው ያሉ የኃይል ተደራሽነት ሥራዎች የማህበረሰቡን ቅሬታ እየፈቱ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በደቡብ ምዕራብ ክልል እያከናወናቸው ያሉ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተደራሽነት ሥራዎች ማህበረሰቡ ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለሚያነሳቸው ቅሬታዎች ተጨባጭ መፍትሔ እየሰጡ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደቡብ ምዕራብ ሪጅን አስታወቀ

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ገብሬ እንደገለፁት ሪጅኑ ከማሻ፣ ቦንጋ፣ አባ እና ሚዛን ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል በመቀበል በደቡብ ምዕራብ ክልል ለሚገኙ ስድስት ዞኖች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ከሚዛን ማከፋፈያ ጣቢያ በስተቀር ከሌሎች ጣቢያዎች በቂ የኃይል አቅርቦት እያገኘ በመሆኑ ደንበኞችን በአግባቡ ማገልገል መቻሉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የሚዛን ማከፋፈያ ጣቢያ የባለ 15 ወጭ መስመር ትራንስፎርመር አቅም በመሙላቱ ምክንያት ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት በሚኖርባቸው ሰዓታት (Peak load) ለደንበኞች በፈረቃ የኃይል አቅርቦት ለመስጠት መገደዳቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጣቢያው ላይ እያከናወነ ያለው የአቅም ማሳደግ ሥራ ሲጠናቀቅ ይህ ችግር ሙሉ በሙሉ እንደሚፈታ እምነታቸውን ገልፀዋል።

አቶ ብርሃኑ አክለውም ከዚህ ቀደም የማሻ ከተማና አካባቢው ከሩቅ ማከፋፈያ ጣቢያ (ከመቱ) ኃይል ያገኝ ስለነበር ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ይከሰት እንደነበርና ይህም በማህበረሰቡ ላይ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማሻ ማከፋፈያ ጣቢያን በመገንባቱ በአካባቢው የነበረው የኃይል መቆራረጥ ችግር ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል።

ይህም ማህበረሰቡ ከቅርበት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኝና ቀደም ሲል ለነበሩ ቅሬታዎች መፍትሄ በመስጠት የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ርቀው ለሚገኙ አካባቢዎች አዳዲስ ጣቢያዎችን በማስፋፋት በሪጅኑ ያለውን የኃይል ተደራሽነት እንዲያጠናክር ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

የኃይል አቅርቦቱን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና ማሰራጫ መስመሮች ላይ ማሻሻያዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ብርሃኑ ለዚህም ሁለቱ ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በሪጅኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኃይል ተደራሽነት ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት እንዲሁም ለምርትና ምርታማነት ማደግ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተገልጿል።

Scroll to Top