ሪጅኑ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ ነው

ሪጅኑ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ ምዕራብ ሪጅን ለደንበኞች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ የሪጅኑ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ቢኒያም ታደሰ ገልፀዋል ።

ተወካዩ እንደተናገሩት በሪጅኑ ከሚገኙ 12 የማከፋፈያ ጣቢያዎች መካከል 10 ተጨማሪ ደንበኞችን የማስተናገድ ሙሉ አቅም ስላላቸው በአሁኑ ወቅት ለሚቀርቡ የኃይል ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ከሁሉም የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በአጠቃላይ ከ134 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ለደንበኞች እየቀረበ መሆኑንም አብራርተዋል።

ሪጅኑ በተለያዩ ምክንያቶች እያደገ ለሚሄደው የኃይል ፍላጎት በአስተማማኝ መልኩ ምላሽ ለመስጠት በጣቢያዎቹ ላይ የአቅም ማሳደግ እና የመቆጣጠሪያ ብሬከሮችን የማዘመን ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም መሠረት በሚዛን ማከፋፈያ ጣቢያ ለባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ኃይል በማቅረብ ላይ የሚገኘውን የትራንስፎርመር አቅም ከ6 ሜጋ ቮልት አምፒር ወደ 12 ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አቶ ቢኒያም አስረድተዋል።

በቀጣይም በጅማ 1፣ በጅማ 2 እና በጊቤ 1 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ተመሳሳይ የአቅም ማሳደግ ሥራዎችን ለማከናወን መታቀዱን ጠቅሰዋል።

የጅማ 2 ማከፋፈያ ጣቢያ በሪጅኑ ለሚገኙ ጣቢያዎች እስከ ጋምቤላና ሚዛን ድረስ እንደ መጋቢ ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑ አሁን ያሉትን የ63 ሜጋ ቮልት አምፔር አውቶ ትራንስፎርመሮች ወደ 125 ለማሳደግ እንዲሁም የባለ 25 ሜጋ ቮልት አምፔር ፓወር ትራንስፎርመሩን ወደ 50 ለማሳደግ ታቅዶ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

በተጨማሪም በጣቢያው ላይ አዲስ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያለው ፓወር ትራንስፎርመር በመትከል የ33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮችን ለማዘጋጀት ታስቧል።

ከአቅም ማሳደግ ሥራዎች ጎን ለጎን የመቱ፣ የበደሌ፣ የጅማ 1 እና የጊቤ 1 የ33 ኪሎ ቮልት የመቆጣጠሪያ ብሬከሮችን በጋዝ ወደሚሰራ የጂ አይ ኤስ (GIS) ቴክኖሎጂ የመቀየር ሥራ ተከናውኗል። በተመሳሳይ የጅማ 1 እና የአጋሮ ባለ 15 ኪሎ ቮልት ብሬከሮችን ከዘይት አሠራር ወደ ቫኪዩም መቀራቸውንም አንስተዋል።

በጅማ ከተማ እየተገነባ ላለው የስማርት ሲቲ አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ የባለ 15 ኪሎ ቮልት የጂ አይ ኤስ ሲዊች ጊር በጅማ 1 ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ መዘጋጀቱንም ተወካዩ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአጋሮ የ33 ኪሎ ቮልት መቆጣጠሪያ ብሬከርን ወደ ጂ አይ ኤስ የመቀየር ሥራ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይም የጋምቤላ፣ የጅማ 2 እና የመቱ ቀሪ ብሬከሮችን ለመቀየር ዕቅድ መያዙን አቶ ቢኒያም ተናግረዋል።

ይህ የማዘመን ሥራ በብሬከሮች ጉድለት ምክንያት የሚፈጠርን የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽንና የቆይታ ጊዜን ለመቀነስ፣ የጥገና ሥራን ለማቃለል እንዲሁም የብሬከር እጥረትን ለመቅረፍ በእጅጉ አግዟል።

በአጠቃላይ በደቡብ ምዕራብ ሪጅን ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ 7 አውቶና 17 ፓወር ትራንስፎርመሮች፣ የቮልቴጅ መዋዠቅን የሚያመጣጥኑ 8 ሻንት ሪያክተሮች እንዲሁም 1 ሺህ 15 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የማስተላለፊያ መስመሮች ይገኛሉ፡፡

Scroll to Top