በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ ምዕራብ ሪጅን በሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚያጋጥሙ የቴክኒክ ችግሮችን በጣቢያዎቹ የውስጥ አቅም የመፍታት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን ሪጅኑ ገለፀ
የሪጅኑ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ቢኒያም ታደሰ እንደገለፀት በማከፋፈያ ጣቢያዎች ለሚያጋጥሙ ድንገተኛ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ስልታዊ አሠራር ተዘርግቷል።
ጣቢያዎቹ የጥገና ሥራዎችን በራሳቸው አቅም ማከናወን እንዲችሉ ለባለሙያዎች ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን አስፈላጊ የመለዋወጫ ዕቃዎችም እንዲሟሉ መደረጉን ገልፀዋል።
በዚህም መሰረት ከሪጅኑ ማዕከል ርቀው በሚገኙ እንደ መቱ፣ ጋምቤላ፣ ሚዛን እና በደሌ ባሉ ማከፋፈያ ጣቢያዎች አብዛኞቹ ድንገተኛ የጥገና ሥራዎች በአሁኑ ወቅት በየጣቢያው ባለሙያዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል ።

የጣቢያ ባለሙያዎች ክህሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለፁት አቶ ቢኒያም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራሳቸው አቅም እየፈቱ እንደሚገኙና ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ውስብስብ ብልሽቶች ሲያጋጥሙ ብቻ በሪጅኑ የጥገና ባለሙያዎች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል።
ከጣቢያዎቹ በጥገና ሥራ ብቃትና ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎችን በመለየት የማበረታቻ ሥርዓት የተዘረጋ ሲሆን ይህም በራስ አቅም የመጠገን ባህል በሁሉም ጣቢያዎች እንዲስፋፋ እያደረገው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚዛን ባለ 132 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊ ወ/ሮ ፀጋነሽ ሞላ በጣቢያው ለሚያጋጥሙ ድንገተኛ ችግሮች የኦፕሬሽን አሰራርን በመከተል እና ያለውን የመለዋወጫ ዕቃ በመጠቀም በራስ አቅም አስቸኳይ መፍትሔ እየተሰጠ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
ቀደም ሲል በጣቢያው ላይ ድንገተኛ ብልሽቶች ሲያጋጥሙ የሪጅን የጥገና ባለሙያዎች እስኪመጡ ድረስ መጠበቅ ግዴታ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊዋ ይህም ለደንበኞች የሚሰጠው የኃይል አቅርቦት ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ እንዲቆይ በማድረግ በተቋሙ የኃይል ሽያጭ ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድር እንደነበር ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን ከውስብስብ የጥገና ሥራዎች በስተቀር የተለያዩ የሜካኒካል ዕቃዎች ብልሽት ሲያጋጥም የጥገና ሥራው በጣቢያው ባለሙያዎች በብቃት እየተከናወነ ይገኛል።
ይህ መሻሻል ቀደም ሲል የሪጅኑ የጥገና ባለሙያዎች በወር እስከ ሁለት ጊዜ ለድንገተኛ ጥገና ያደርጉት የነበረውን ጉዞ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰው ሲሆን አሁን ላይ ከሲቲ (CT) እና ቪቲ (VT) ጋር የተገናኙ እና መሰል ከባድ ጥገናዎች ካላጋጠሙ በስተቀር ከሦስት እስከ ስድስት ወር ድረስ ወደ ጣቢያው የማይሄዱበት አጋጣሚ መፈጠሩን ወ/ሮ ፀጋነሽ አስረደረተዋልል።
በአጠቃላይ ድንገተኛ የጥገና ሥራዎች በየጣቢያዎቹ አቅም መከናወናቸው የሪጅኑ የጥገና ባለሙያዎች እስኪደርሱ ድረስ ኃይል ተቋርጦ የሚቆይበትን ጊዜ በማሳጠር የሪጅኑን የሀብት አጠቃቀም በማሻሻል እና ተቋሙን ከተጨማሪ ወጪዎች በመታደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የሥራ ኃላፊዎቹ አብራርተዋል።




