ያለፉት ሰባት ዓመታት በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው –  ተስፋሁን ጎበዛይ

ያለፉት ሰባት ዓመታት በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው –  ተስፋሁን ጎበዛይ

በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስኬቶች መመዝገባቸውን  የኢፌዲሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለፁ።

ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራሮችና ሠራተኞች “መሀሉ ዘመን” በሚል መሪ ሀሳብ በመንግስት የተዘጋጀውን የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ እንደገለፁት መሀሉ ዘመን የኢትዮጵያን መነሻ፣ አሁን የደረሰችበትን ሁኔታ እና ቀጣይ መዳረሻ የሚያመላክት የሽግግር ዘመን ነው ብለዋል።

ከትላንት ውድቀቶቻችንና ከዛሬ ስኬቶቻችን ተምረን ነገን የተሻለ ለማድረግ እንደ ሀገር ጠንክረን  መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ፈተናዎችን መሻገሯን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የበረሃ አንበጣና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭትና መፈናቀል ለውጡን የፈተኑ ጉዳዮች መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በለውጡ ዋዜማና በለውጡ ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እንዲሁም ስኬቶችን አብራርተው በዓለም ሀገራት የኃይል አሰላለፍ ውስጥ የኢትዮጵያ አቅም እንዴት እንዳደገና ምን ውጤት እንደመጣም ገልፀዋል።

ያለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስኬቶች የታዩበትና መዋቅራዊ ለውጥ የተደረገበት  መሆኑንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት፣ የአመራሩ ቁርጠኝነት እና ብስለት የተሞላበት ውሳኔ ለውጡን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

የሕዝብ ጥያቄዎችን በመመለስ፣ የትርክት ለውጥ በማምጣት፣ አካታች ፖለቲካዊ አጀረጃጀት እና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም በመተግበር ስኬት ማስመዝገብ መቻሉንም ነው የገለፁት።

እንደ አቶ ተስፋሁን ገለፃ የተሳካ የህግ ማስከበር ዘመቻ፣ የፕሪቶሪያ ሥምምነት እና የህዳሴ ግድብ እያደገ ለመጣው የኢትዮጵያ አቅም አወንታዊ ሚና ተጫውተዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረሱ ለኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ብርሃን የፈነጠቀና  በቀጣናው ሀገራት ላይም ያላትን የኃይል ሚዛን ያስጠበቀ መሆኑን ገልፀዋል።

ተቋሙ በኃይል ልማት ዘርፉ ላይ እያከናወናቸው የሚገኙትን የለውጥ ሥራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ በማሳለጥ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን ለማሻሻል መስራት እንደሚገባው ጠቅሰዋል።

በቀረበው ሰነድ ላይ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል።

የባህር በር ጥያቄው ተቋሙ በኃይል ልማት ዘርፉ ለሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች የሚያገለግሉ ግብዓቶች በወቅቱ ወደ ሳይት እንዲደርሱ በማድረግ በአፈፃፀማቸው ላይ አወንታዊ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ኢንጂነር አሸብር ጠቅሰዋል።

በኦፕሬሽን እና ግንባታ ሥራዎች ላይ ውጤታማ ለመሆን እንደ ተቋም ያለውን አቅምና ግብ ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባት እንደሚያስፈልግ አፅዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የተቋሙ አመራር እና ሠራተኛ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ የሆነውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለመመለስ መስራት እንደሚገባ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሳስበዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top