በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ወጭ ቆጣቢ፣ የሥራ ጥራት እና ቅልጥፍና መለያቸው እንዲሆነ እየተሰራ መሆኑን በተቋሙ የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጅነር ውድነህ የማነ ገለጹ።
ዘርፉ የ2018 በጀት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን ሲገመግም ኢንጂነር ውድነህ እንደተናገሩት ባለፉት ስድስት ወራት በኢንጅነሪንግ ዲዛይን፣ በመነሻ ዲዛይን፣ በፕሮጀክቶች ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ተግባራት ላይ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ
በበጀት ዓመቱ የክፍያ የይገባኛል ጥያቄና የጊዜ ማራዘሚያ በማዘጋጀት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ከማጠናቀቅ፣ ለተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች የመዝጊያ ሪፖርት ከመስራት፣ ከእቃ አቅራቢዎች ጋር በመነጋገር ሠራተኞች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ከማድረግ አኳያ በጥንካሬ መገምገማቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የፕሮጀክቶችን መሠረታዊ ችግሮች በመለየት፣ አፈጻጸማቸውን ወጥነት ባለው መንገድ በመገምገም የተሻለ የግንባታ አፈፃጸም እና የፋይናንስ ቁመና እንዲኖራቸው መደረጉን ጠቁመዋል።
ሆኖም ከአዳዲስ የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ዝርዝር የአፈር ምርመራ ውጤት ትንተና፣ አዳዲስና ነባር የማስተላለፊያ መስመር ታወር የመሰረትና የአፈር ምርመራ ሥራዎች፣ የማማከር ውል ስምምነቶችን ከማዘጋጀትና ማደስ አኳያ ዝቅ ያለ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ መመዝገቡን አንስተዋል፡፡



በበጀት ዓመቱ የግንባታ እቃ አቅርቦቶችን በጊዜ ከማድረስ፣ ለግንባታ ሥራ በባለቤቱ ለሚቀርቡት እቃዎች የተጠናቀቀ ዲዛይን ከመስጠት፣ ለባለሙያ እና ለመስሪያ መሣሪያዎች እጥረት በወቅቱ መፍትሄ ከመስጠት አንጻር ክፍተቶች መስተዋላቸውንም አስገንዝበዋል፡፡
እንደ ኢንጅነር ውድነህ ገለፃ በእቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶች የጥናት ሰነድ በጊዜ አለመጠናቀቅ፣ የነዳጅ ችግር፣ የኤሌክተሮ መካኒካል እና የሌሎች እቃዎች አቅርቦት መዘግየት፣ በዘርፉ ውስጥ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች አሮጌ መሆን በበጀት ዓመቱ ዘርፉን የፈተኑ ችግሮች ናቸው፡፡
በመጀመሪያው ግማሽ የበጀት ዓመት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማጠናከር እንዲሁም ክፍተቶችን በማረም በቀሪ ስድስት ወራት የተሻለ አፈጻጸም ለመስራት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዘርፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሟላ ሥራ ተቋራጭ ለመሆን ከያዘው ዕቅድ አንፃር ትርፋማ መሆን እና ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠይቃል ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለዚህ ደግሞ ሁሉም ሠራተኛና አመራር በቁርጠኝነትና በጊዜ የለኝም መንፈስ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የቀረበውን ሪፖርት መሰረት በማድረግ ከፕሮጀክት ክትትልና ቁጥጥር፣ ከፋይናንስ፣ ከትራንስፖርትና ከማሽነሪ አቅርቦት፣ ከአቅም ግንባታ እና ከቅጅታዊ አሰራር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ተነስተው በሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



