የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቱ ከ40 በመቶ በላይ ደርሷል

የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቱ ከ40 በመቶ በላይ ደርሷል


ለደሴ ከተማና አካባቢው አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ታስቦ እየተገነባ የሚገኘው የደሴ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት አጠቃላይ አፈፃፀሙ 40 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አስታወቁ፡፡

አስተባባሪው አቶ አብዲ ኪያር እንዳስታወቁት የፕሮጀክቱ የአፈር ቆረጣና ልል አፈር የማንሳት ሥራ ከተያዘለት ጊዜ በላይ ቢወስድም ሥራውን በታቀደለት ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ማከፋፈያ ጣቢያው እያንዳንዳቸው 63 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች እንዲሁም ስድስት ባለ 33 እና አስር ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች እንደሚኖሩት ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱን የግንባታ ሥራ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አብዲ አማካሪና ሥራ ተቋራጩ በአንድ ዘርፍ ስር መሆናቸው ዲዛይኖቹን በወቅቱ እንዲቀርቡ እና ሥራዎች በቅንጅት እንዲከናወኑ በማድረግ ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት እንደሚያግዝም አስታውቀዋል፡፡

የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የደሴ ከተማ የመስተዳድር አካላት ክትትልና የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሆነ ተናግረው ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮቹን በወቅቱ በመፍታት ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ የክትትልና ድጋፍ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

በፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ዘለቀ አድነው በበኩላቸው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች መሬት ላይ የሚቀበሩ የተለያዩ የመከላከያና ሌሎች ሥራዎችን ጨምሮ የተከላ፣ ፍተሻና ሙከራ ሥራዎችን እንደሚያጠቃልል በመግለጽ በአሁኑ ወቅትም ትራንስፎርመሮች ቦታቸው ላይ ተቀምጠው የገጠማ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በትራንስሚሽን ቢዝነስ የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምሩ ባቱ እንደተናገሩት የፕሮጀክቱ የግንባታና የማማከር ሥራ በተቋሙ የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ በመከናወን ላይ ሲሆን ሲዩዋን የተሰኘው የቻይናው ኩባንያ ደግሞ በኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች አቅርቦት ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ በራስ ኃይል መከናወኑ ተቋሙን ከተጨማሪ ወጭዎች ከማዳኑም ባለፈ ሥራውን በባለቤትነት ስሜት ለማከናወን እና የእውቀት ሽግግር በማምጣት ተቋማዊ አቅምን ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማከናወን ዕቃዎች በጥር ወር ላይ እንዲገቡ ከአቅራቢው ጋር ስምምነት ተደርሶ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም ከ40 በመቶ በላይ መድረሱን በመጠቆም የግንባታ ሥራውን በተያዘለት ዕቅድ ለማጠናቀቅ የክትትልና ድጋፍ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top