የኮምቦልቻ ቁጥር 3 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት በመጠናቀቀ ላይ ይገኛል

የኮምቦልቻ ቁጥር 3 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት በመጠናቀቀ ላይ ይገኛል

የባህርዳር – ወልዲያ ኮምቦልቻ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የኮምቦልቻ ቁጥር 3 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የጣቢያው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ተቆጣጣሪ ተናገሩ፡፡

ተቆጣጣሪው አቶ ኃይለኢየሱስ ስንታየሁ እንደተናገሩት ማከፋፈያ ጣቢያው በ400 ኪሎ ቮልት በኩል 1000 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል የመሸከም አቅም ያላቸው ሁለት አውቶ ትራንስፎርመሮች እንዲሁም በ230 ኪሎ ቮልት በኩል 300 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ሁለት ፓወር ትራንስፎርመሮች አሉት፡፡

በተጨማሪም ጣቢያው 20 ባለ 33 እና ሁለት ባለ 230 ኮሎ ቮልት ወጭ መስመሮች እንዳሉት ገልፀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ እና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የግንባታ ሥራዉ ቢጓተትም በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሮ ሜካኒካል የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

450 ሜጋ ዋት ኃይል የመሸከም አቅም ያለው ይህ ጣቢያ የቁጥጥር ሥራውን የሚያቀላጥፉ እና ደህንነቱን የሚያስጠብቁ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንደተገጠሙለትም ተናግረዋል፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለአዋሽ -ወልዲያ- ሀራ ገበያ የባቡር መስመር፣ ለኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም ለከተማዋና አካባቢው አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል አቶ ኃይለኢየሱስ ጠቁመዋል፡፡

የመጀመሪያ ዙር የፍተሻና ሙከራ ሥራዎች ተጠናቀው ሁለተኛውን ዙር ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ያስረዱት አቶ ኃይለኢየሱስ ጣቢያውን ወደ ሥራ ለማስገባት የባህርዳር- ወልዲያ – ኮምቦልቻ የማስተላለፊያ መስመር እና የወልዲያ ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሥራ መጠናቀቅን እንደሚጠብቅ አንስተዋል፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያው የሲቪል ሥራዎች ተቆጣጣሪ አቶ ምኒሊክ ሰለሞን በበኩላቸው ከሲዊችያርድ የጠጠር ማልበስ፣ ከውስጥ ለውስጥ መንገድ እና ከአጥር ሥራዎች ውጭ ሌሎች የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በተለያዩ የግንባታ ምዕራፎች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ያስታወሱት ተቆጣጣሪዎቹ በፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ላይ የተሳተፉ የተቋሙ ሠራተኞችና የአካባቢው ወጣቶች በቀጣይ ለሚከናወኑ ተመሳሳይ ሥራዎች ዕውቀት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top