የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም የሚያዘገዩ የግዥና የቴክኒክ ማነቆዎችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ የተቋሙ የሥልጠና ኢንስቲትዩትና የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ገለፁ።
በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ለሠራተኞች በተዘጋጀው ሥልጠና ላይ ሥራ አስኪያጁ አቶ እንዳለ የሺጥላ እንደገለፁት ሥልጠናው ከመንግሥት መደበኛ የግዥ ፖሊሲዎች ባሻገር ከዓለም አቀፍ የግዥ ደንቦች ጋር የሚጣጣም ዕውቀትና ልምድ ለማዳበር ያግዛል፡፡


ተቋሙ የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች በግዥ ሂደቶች እንዳይዘገዩ ሥልጠናው ክፍተቶች ለመዝጋት ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናው ግልፅ ደንቦችን በማዘጋጀት፣ የኮንትራት አስተዳደርን በማጠናከር፣ የድርድር ክህሎትን በማሳደግና የግዥ አሰራሮችን በማቀላጠፍ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብና ጥራት እንዲጠናቀቁ እንደሚረዳም አመልክተዋል፡፡

እንደ አቶ እንዳለ ገለፃ ሥልጠናው ሠራተኞች ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የህግ ማዕቀፎችን ተረድተው በሥራ ላይ እንዲተገብሯቸው ያስችላቸዋል፡፡
ከሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የግዥ መመሪያዎች ጋር የተጣጣሙ አዳዲስ አሰራሮች የፕሮጀክት አፈፃፀም መዘግየትን በመቅረፍ ግዥዎች ያለእንቅፋት እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል፡፡
በግዥ አፈፃፀም ሂደት የሚሳተፉ ሠራተኞችና አመራሮች ወቅታዊ ህጎችን እንዲያውቁ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

